በሎሬት ጸጋየ ገብረ መድኅን ስም የተሰየመው እና በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው የሎሬት ጸጋየ ገብረ መድኅን የባህል ጥናት እና ምርምር ማእከል 552 ከያኒያንን በሁለት አመት ውስጥ ስልጠና እንዲያገኙ ማድረጉ ተገለጸ።
ይህን የገለጹት ከሃገሬ ቴ.ቪ ጋር ቆይታ ያደረጉት የማእከሉ ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ለይኩን ናቸው።
አቶ ሳሙኤል የባህል ጥናት እና ምርምር ማእከሉ የሎሬት ጸጋየ ገብረ መድኅንን የኢትዮጵያዊነት እሳቤ ለከያኒያኑ ለማስተላለፍ እንደሚሰራም ገልጸውልናል።
በማእከሉ በጥበባዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚሳተፉ ወጣቶች እና አዳጊዎችም ተሰጥኦዋቸውን እንዲያዳብሩ እንዳገዛቸው ነግረውናል።
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው የሎሬት ጸጋየ ገበረ መድኅን የባህል ጥናት እና ምርምር ማእከል የአካባቢው ባህል፣ ቋንቋ እና ትውፊትን ለመጭው ትውልድ ለማስተላለፍ እየሰነደ ስለመሆኑም ነግረውናል።
የማእከሉ ሃላፊ እንደገለጹልን ማእከሉ የባህል ጥናት እና ምርምር ላይ ከመስራቱ በተጨማሪም በሎሬት ጸጋየ ገብረ መድኅን ስም እንደመመስረቱ ልጆች እና ወጣቶችን በጥበቡ ዘርፍ ከብሄራዊ ቴያትር ጭምር ጋር በመተባበር አሰልጥኖ እያበቃ ነው።
“ ከአምቦ እና አካባቢው ለመጡት ልጆች በሙዚቃ፣ በቴያትር፣ በተውኔት አጻጻፍ፣ በስእል እና ቅርጻ ቅርጽ ፣ በዳንስ ፣ በሞዴሊንግ እና ዲዛይን በሰባት ዘርፎች እያሰለጠንን ነው ያለነው።”
የጥበብ ዝንባሌ ያላቸው የአካባቢው ልጆች እና ወጣቶችን ስልጠና እንዲያገኙ ከማድረጉም በተጨማሪ ስራዎቻቸውን በተለያዩ መድረኮች ማቅረብ እንዲችሉ እያደረገ ስለመሆኑም ነግረውናል።
በሎሬት ጸጋየ ገብረ መደኅን ስም የተመሰረተው ማእከሉ የሎሬቱን የኢትዮጵያዊነት እሳቤ ለከያኛኑ ለማስተላለፍም እየተሰራ እንደሆነ ገልጸውልናል።
የባህል ጥናት እና ምርምር ማእከሉ በተለይም ከልጆች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ከያኒያንን ስልጠና እንዲያገኙ የሚያደርግ ሲሆን እስካሁን ከተመሰረተ ሁለት አመቱ ቢሆንም በተለያዩ የጥበብ ዘርፎች 552 ልጆች እና ወጣቶችን ስለማሰልጠኑ የማእከሉ ሃላፊ ነግረውናል።
በማእከሉ ውስጥ በሙዚቃ፣ በትወና፣ በስእል፣በውዝዋዜ፣ በዳንስ ብሎም በሌሎች ጥበባዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ከሚሳተፉት አባላት መካከልም ማእከሉ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ከማድረጉም በተጨማሪም መልካም አዋዋል እንዲኖረን አድርጓል ሲሉ ለሀገሬ ቴ.ቪ ተናግረዋል።
አቶ ሳሙኤል እንደነገሩን ማእከሉ ልጆች እና ወጣቶቹን ክህሎታቸውን እንዲጠቀሙበት ለማድረግ እየሰራ ስለመሆኑ ነግረውናል።
የማእከሉ ሃላፊ የሎሬት ጸጋየ ገብረ መድኅን ለኢትዮጵያ ጥበብ አበርክቶው ትልቅ ቢሆንም በቂ መታሰቢያ አልተደረገለትም ይላሉ።
“በርግጥ በጸጋየ ስም ማእከል መክፈት፣ በጸጋየ ስም ሃውልት ማቆም ጸጋየን አይጠቅመውም፤ ይልቁንስ ያሁኑ ትውልድ ነው ከዚያ መጠቀም የሚችለው።’’
አቶ ሳሙኤል ለይኩን የጸጋየ እሳቤን ማጥናት እና ለትውልድ ማስተላለፍ ሰላም እና መቻቻላችንን ለመመለስ የራሱ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላል ባይም ናቸው።
በአብርሃም በለጠ
2022-06-03
