ሀገሬ ቲቪ

100ኛ ቀን ያስቆጠረው ጦርነት

በዩክሬን እና በሩስያ መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ዛሬ መቶኛ ቀኑን አስቆጥሯል፡፡

በእነዚህ አንድ መቶ የመከራ ቀናት ከ ሁለቱ ሀገራት አልፎ አለማችን ላይ ያልታሰበ ጣጣ ይዞብን መጥቷል ። በርካታ ንጹሀን ከ ቀያቸው ተሰደዋል ከቤተሰባቸው ተለይታዋል ብሎም ህይወታቸውን አጥተዋል። ከዛም አልፎ እንዚህ አንድ መቶ ቀናት የ አለማችንን ኢኮኖሚ በ እጅጉ ፈትነዋታል ።

ቀውሱ ዛሬም ቀጥሏል ለጊዜው ዩክሬን የኔቶ አባል ባለመሆኗ፣ ኔቶ በቀጥታ በጦርነቱ ላይ በመሳተፍ ከራሽያ ጥቃት ሊያስጥላት ባይችልም፣ የኔቶ አባል አገራት የሆኑት አሜሪካ እና አጋሮቹ በበኩላቸው የጦር መሳሪያ እና የታክቲካዊ መረጃ ወደ ዩክሬን በመላክ ድጋፍ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።

ሆኖም የሩሲያ ጎረቤት ሀገራት ፊንላንድ እና ሲውዲን ኔቶን ለመቀላቀል መወሰናቸው በኔቶ ጦር እና በሩሲያ ጦር መካከል ያለውን ፍጥጫ የማይቀር ያስመስለዋል።

ለመሆኑ የኔቶ ወታደራዊ ጥምረት ምን ያህል ጠንካራ ነው።? የፑቲን ጦርስ የኔቶን ሀይል መቋቋም ይችል ይሆን ?

በስታቲስታ ምርምር ዲፓርትመንት፣ ማርች 3፣ 2022 በታተመ ዘገባ፣ የኔቶ ጦር ከሩስያ ጦር ጋር ያለው ንጽጽር ይህን ይመስላል ።

ኔቶ በግምት 3.37 ሚሊዮን ወታደሮች በተጠንቀቅ አሉት፣ ለዚህም አሜሪካ ሰፊውን ድርሻ ትይዛለች ። በጥናቱ መሰረት አሜሪካ 1.4 ሚሊዮን ንቁ ወታደሮች, እንዲሁም 865,000 ተጠባባቂ ወታደሮች ሲኖሯት ፣ የዩናይትድ ስቴትስ አመታዊ የመከላከያ ወጪም 705 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነም ይገመታል፣ ይህ ማለት ሌሎች የኔቶ አገራት ቢደመሩ በእጥፍ የሚበልጥ ቁጥር ነው።

ራሽያ በበኩሏ 1.35 ሚሊዮን ወታደሮች ሲኖሯት፣ አመታዊ የመከላከያ ወጪዋም ወደ 42 ቢሊዮን ዶላር እንደሚጠጋ ጥናቱ ያመለክታል ።

ጥናቱ የመሳሪያ አቅማቸውን ሲያነጻጽር ኔቶ 20,723 ጀቶች ሲኖሩት ሩሲያ 4,173 ናቸው፣ በባህር ኃይልም ፣ ኔቶ 2,049 ወታደራዊ መርከቦች ያሉት ሲሆን በሩሲያ በኩል 605 ወታደራዊ መርከቦች አሉ ። የመሬት ላይ የውጊያ ተሸከርካሪ አቅማቸውን ብንመለከት ኔቶ 12,420 ክፍሎች ያሉት ሲሆን ሩሲያ ግን የ14,682 የመሬት ላይ የውጊይዝ ተሽከርካሪ ባለቤት ናት ።

ታዲያ እነዚህን ቁጥሮች ስንመለከት ኔቶ የበለጠ ጠንካራ ቢመስልም በሩሲያ በኩል ግን ሌላ አንድ አስፈሪ ኃይል አለ፣ የሩሲያ የኑክሌር ኃይል።

የዩናይትድ ስቴትስ፣ የዩናይትድ ኪንግደም እና የፈረንሳይ ጥምር የኒውክሌር ጦር መሳሪያ 6,065 ኒውክሌር ጦሮች ሲደርሱ ፣ ሩሲያ ለብቻዋ 6,255 የኒውክሌር ረጅም ርቀት የጦር መሳሪያዎች አሏት ፣ በዚህ ብቻ አያበቃም፣ ለ አሜሪካም ለኔቶም ከፍተኛ ስጋት የሆኑት ፣ የ ሩስያ የጦር ሚሳይሎች በብዛት ብቻ ሳይሆን በአይነትም ብልጫ አላቸው።

እነዚህ የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች በከፍተኛ ፍጥነት ወይም በሃይፐርሶኒክ speed ረጅም ርቀት መጓዝ የሚችሉ ሲሆን በአንድ ጊዜ ጥቃትም ዩናይትድ ኪንግደምን ጸጥ ረጭ ሊያረጓት ይችላሉ።

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያ በሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎች ላይ የምታደርገውን ኢንቨስትመንት ደጋግመው ገልጽዋል። እነዚህ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎች ከድምጽ ፍጥነት ከአምስት እጥፍ በላይ ሊጓዙ ይችላሉ።ኪንዝሃል የተሰኙት እነዚህ ሚሳይሎች እስከ 2,000 ኪሜ ርቀት ላይ ኢላማውን ሊመታ እና በሰአት ከ6,000 ኪሎ ሜትር በላይ መብረር ይችላሉ።

ባለፈው ታህሳስ ወር ሩሲያ በሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎች አለምን እየመራች ነው ሲሉ ፉከራ ያደረጉት ፕሬዝዳንት ፑቲን፣ሚሳይሎቹ በበረራ አጋማሽ ላይ አቅጣጫ መቀየር ስለሚቻል ለመከታተል አስቸጋሪ ነው ብለዋል።

ታዲያ አሁን ባለው ሁኔታ ታላላቅ ወታደራዊ ኃይሎች፣ ፊት ለፊት መጋፈጥ ግዴታቸው ይሆናል ። ከዛም ብሶ የኒውክሌር ጦር መሳሪያውች ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉበት መንገድ ሰፊ ነው ። ከዚህ ሁሉ ወድመት ግን ይህ ቀውስ በዲፕሎማሲያዊ መልኩ እንዲያበቃ የሁላችንም ጸሎት ነው ።

በዮሴፍ ከበደ
2022-06-03