ሁበር ኢትዮጵያ የትራንስፖርት እና የዴሊቨሪ አገልግሎቴን መስጠት ጀምሬያለሁ አለ።
ሁበር ኢትዮጵያ አገልግሎቴን በተሻለ መንገድ ይሰጥልኛል ያለውን የሞባይል መተግበሪያ በትላንትናው ዕለት ይፋ አድርጓል።
በመላው ኢትዮጵያ አገልግሎቱን ለማዳረስ በርካታ ስራዎችን አስቀድመው ስለመሰራታቸውም በመድረኩ ተነስቷል።
6 የተለያዩ አገልግሎቶችን በአንድ መተግበሪያ በማቀፍ ለተጠቃሚዎቼ አቅርቢያለሁ ብሏል ሁበር ኢትዮጵያ።
ትራንስፖርት፣ እቃዎችን ማድረስ፣ ባለሙያን ማገናኘት፣ መድሀኒት፣ ምግብ እና አስቤዛን ተጠቃሚዎች ባሉበት ሆነው የሁበር ኢትዮጵያን መተግበሪያ በመጠቀም ማግኘት የሚችሏቸው አገልግሎቶች መሆናቸውንም ለማወቅ ችለናል።
ከ20 በላይ በሆኑ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ አገልግሎቱ ተደራሽ መሆኑ ሁበር ኢትዮጵያን ተመራጭ ያደርገዋልም ነው የተባለው።
ተቋሙ ስራውን ሲጀምር በርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በማካተት ስለመሆኑ ያነሱት የሁበር ኢትዮጵያ ኦጵሬሽን ማናጀር አቶ በኃይሉ ደሳለኝ ተናግረዋል።
“ሁበር ኢትዮጵያ በአጭር ግዜ ውስጥ ወደ 2,500 የትራንስፖርት ሰጪዎችን፣ 90 መድሀኒት ቤቶች፣ 80 ምግብ ቤቶች እና 30 ሱፐር ማርኬቶች በሁበር የሞባይል መተግበሪያ አገልግሎታቸውን ለማቅረብ ተስማምተዋል”
ሁበር ኢትዮጵያ የጀመረው አገግሎት ለማህበረሰቡ የበለጠ ጠቀሜታን የሚሰጥ መሆኑም በማብሰሪያ መድረኩ ላይ ተነስቷል።
የክብር እንግዳ በመሆን በመድረኩ የተገኙት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክትር አቶ እሎሞን ሶካ እንዳሉት ከሆነ፤ እንደ ሁበር ያሉ ተቋማት ወደ ኢንዱስትሪው መቀላቀላቸው ለማህበረሰቡ የተሻለ ጠቀሜታን ያስገኛል።
በተለይ ሁበር የተለያዩ አገልግሎቶችን አካቶ መምጣቱ የተሻለ ፉክክርን ለመፍጠር ያግዛል።
“ልክ እንደ ሁበር ያሉ የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት ብቻም ሳይሆን የእቃዎች ማድረስ አገልግሎትን የመሳሰሉ ሌሎች አገልግሎቶችን በማካተት፤ አድማሳቸውን ጭምር በማስፋት በመላው ኢትዮኦጵያ ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት የሚደገፍ ነው።”
ሁበር ኢትዮጵያ በዘርፉ ያለውን የትራንስፖርት አገልግሎት ክፍተት በሚገባ መሙላት የሚችል መሆኑም በመድረኩ ተነስቷል።
በማብሰሪያ መድረኩ አገልግሎት ሰጪዎችን፣ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን እና የትራንስፖርት ፈላጊዎችን በአንድ ላይ ማስተሳሰር የሚችል የሞባይል መተግበሪያ ይፋ ሆኗል።
በማብሰሪያ ፕሮግራሙ ላይ ሁበር ኢትዮጵያ ወደስራ ለመግባት በተጓዘባቸው መንገዶች ሁሉ አወንታዊ ሚናን ለተጫወቱ አካላት ሁሉ የምስጋና መርሃግብርን አድርጓል።
በሳምሶን ገድሉ
2022-06-06
