የአረብ ሃገራቱ ግብጽ፣ ሶሪያ እና ሌባኖን ላይ እስራኤል ላይ የቅድመ መከላከል ያለችውን ጦርነት ከፍታለች። ነገሩ የሆነው ከዛሬ 55 አመታት በፊት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1967 ነው። ለስድስት ቀናት በቆየው በዚህ ጦርነት እስራኤል በአረብ ሃገራቱ ላይ ድል መቀዳጀት ችላለች። የዛሬው እለቱን ከታሪክ በዚሁ የስድስት ቀናቱ ጦርነት ላይ ትኩረቱን ያደርጋል።
ግማሽ ክፍለ ዘመንን መለስ ስንል በመካከለኛው ምስራቅ የተከሰተውን የስድስቱን ቀን ጦርነት እናገኛለን። ይሄው በእስራኤል እና በአረብ ሃገራቱ መካከል የተደረገው ጦርነት በተካሄደበት ወርህ የጁን ጦርነት ብሎም ሶስተኛው የአረብ እስራኤል ጦርነት ተብሎ ይታወቃል። በኛ 1940 እስራኤል በመካከለኛው ምስራቅ እንደአገር መመስረቷን ካወጀች ጀምሮ ጎረቤቶቿ የአረብ ሃገራት በይሁንታ አልተቀበሏትም።
ግና ከስድስቱ ቀናት ጦርነት አስቀድሞ የተደረጉት ሁለት ጦርነቶችም ይሁኑ ትንንሽ የድንበር ላይ ግጭቶች እስራኤልንን እንደሃገር ከመቀጠል አላስቆሟትም።
ወደ ስድስቱ ቀን ጦርነት ሲንደረደሩም ፓሌስታንያውያን ከሶሪያ እስራኤል ላይ የሽምቅ ውጊያ መክፈታቸው የሁለቱን ሃገራት ውጥረት አባብሶታል። ክስተቱ ከሁለቱም በኩል የተሳሳቱ ስሌቶች እንዲኖሩ አደረገ። ሶሪያ በእስራኤል እወረራለሁ የሚል ስጋት ስላደረባት ከግብጽ እገዛን ጠየቀች። ግብጽ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጸጥታ አስከባሪዎች ከሲናይ ልሳነ ምድር እንዲወጡ በማድረግ ወታደሮቿን ወደ ቀጠናው በማስገባት ምላሽ ሰጠች።
ከሁለቱም ወገን ወታደራዊ ዛቻዎች ጨመሩ። ግብጽ ከጆርዳን ጋር ወታደራዊ ስምምነት ተፈራረመች። የሶቭየት የስለላ ሪፖርት እስራኤል ወደ ሶሪያ የመዝመት እቅድ እንዳላት አስታወቀ። የግብጹ ፕሬዝዳንት ጋማል አብደል ናስር የግብጽን ጦር ለጦርነት እንዲዘጋጅ አነቃቂ ንግግር አደረጉ።
ቀድሞም ከእስራኤል መተማመን የሚያጥረው ቀጠናው ድባብ ያሰጋት እስራኤል የቅድመ መከላከል ጥቃትን ቅድሚያውን ወደ ግብጽ አድርጋ በሶስቱ የአረብ ሃገራት ላይ የአየር ጥቃት ከፈተች። በድንገተኛ ጥቃቱ ግብጻውያንን በማስደንገጥ 18 የተለያዩ የአየር አውሮፕላኖችን በመምታት 90 በመቶ የሚሆነውን የግብጽ አየር ሃይል መሬት ላይ እንዳለ አወደመች። ከዚያም እስራኤል ጥቃቷን ወደ ዮርዳኖስ፣ ሶሪያ እና የኢራቅ አየር ሃይሎች አሰፋች።
በስድስት ቀናት ውስጥ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከጁን 5 እስከ 10 1967 ባለው ጊዜ የእስራኤል ጦር የሲናይ ልሳነ ምድርን፣ የጋዛ ሰርጥን፣ ዌስት ባንክን፣ የዮርዳኖስ ወንዝን፣ ምስራቃዊ ኢየሩሳሌምን ብሎም የጎላን ኮረብታዎችን ተቆጣጠረ።
በሰባተኛው ቀን በጁን 11 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ ሲሆን በስድስት ቀናቱ ጦርነት እስራኤል ራሷን ከእጥፍ በላይ አሳድጋለች። የሲናይ ልሳነ ምድርን ከግብጽ፣ የጎላን ኮረብታዎችን ከሶሪያ፣ ዌስት ባንክን እና ምስራቅ ኢየሩሳሌምን ከጆርዳን ነጥቃለች።
የጸጥታው ምክር ቤት እስራኤል ከያዘቻቸው ግዛቶች እንድትለቅ ቢልም እስራኤል ውሳኔውን ውድቅ በማድረግ በያዘቻቸው ስፍራዎች ላይ ወታደራዊ አስተዳደር መስርታለች። የጎላን ኮረብታዎች እና ምስራቃዊ ኢየሩሳሌም ወደ እስራኤል በመደበኛነት ተከልለዋል። ጋዛ ሰርጥ እና ዌስት ባንክ እስራኤል በወታደራዊ ቁጥጥር ስር እንዲሆኑ አደረጋለች። የሲናይ ልሳነ ምድር ብቻ በእስራኤል ግብጽ ስምምነት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1982 ግብጽ ለእስራኤል ዲፕሎማሲያዊ እውቅና በመስጠቷ ተመላሽ ሆኗል። ሌሎቹ ግዛቶች ግን ሊሎቹም ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ እውቅና እስኪሰጥዋት በመያዣነት በእስራኤል እጅ ናቸው።
ከስድስቱ ቀናት ጦርነት በኋላ የአረብ መሪዎች በመካከለኛው ምስራቅ እጣ ፈንታ ላይ በመከሩበት ከእስራኤል ጋር ሰላምም፣ ስምምነትም፣ እውቅና መስጠትም የለም ሲሉ ብሎም በተያዙት ግዛቶች ላይ የፍልስጤማዊ አረቦችን መብት ለማስጠበቅ ስምምነት አድርገዋል።
በ21ኛው ክፍለ ዘመን ጭምር በስድስቱ ቀን ጦርነት በተያዙት ግዛቶች ላይ ፍልስጤማውያን ነጻ ግዛት ለመመስረት መጣራቸው ብሎም የኢየሩሳሌም አከራካሪነት ትልቅ ፖለቲካዊ ጉዳይ ሆኖ ዘልቋል።
የመካከለኛው ምስራቅን ፖለቲካዊ ካርታ መቀየር በቻለው እና እስራኤል ከፍተኛ ድል በተቀዳጀችበት በዚህ የ132 ሰዐታት ጦርነት 20 ሺህ አረቦች እና 800 እስራኤሎች ህይወታቸውን አጥተዋል። የግብጹ ጋማል አብደል ናስር በኀፍረት ስልጣናቸውን እንዲለቁም ምክንያት ሆኗል።
በአብርሃም በለጠ
2022-06-06
