የሰው ልጅ በሀገሬ አጠራር ለ አቅመ አዳም ሲደርስ የትዳር አጋር መያዙ አይቀሬ ነው ።
ታዲያ በትዳር አለም ውስጥ የሚፈጠሩትን አለመግባባቶች ተነጋግሮ መፍታት ጋብቻን ረጅም ጊዜ እንዲያቆይ ከሚያረጉ ነገሮች ውስጥ አንዱ ነው። ዛሬ አንድ ብራዚላዊ በፍቅር መሀል በተፈጠረ ግጭት በመበሳጨት ያደረገው ድርጊት ቢያስገርመን ልናካፍችሁ ወደድን። ግለሰቡ በ አንድ ወቅት ወድጃታልሁ ካላት ካልዳስ ከተባለች የ18 ዓመት ታዳጊ ጋር የፍቅር ግንኙነት ይጀምራል።
በ ፍቅር ግንኙነታቸው አመታትን ቢያሳልፉም በመሀላቸው በተፈጠረ አለመግባባት ከ ሴቷ በኩል ካሁን በኋላ አልፈልግህም የሚል መልዕክት ይደርሰዋል ።ወጣቱ በመሀላቸው የተፈጠረውን ቅራኔ ለመቅረፍ ብዙ ቢጥርም ተፈቃሪዋ ውሳኔዋን ልትሽር አልቻለችም ።በዚህ የተበሳጨው አፍቃሪም በበቀል መንፈስ አንድ አስከፊ ነገር ለማድረግ ወሰነ ። ቀጥሎም የበፊት ፍቅረኛው ካልዳስ ወደ ትምህርት ቤት በምትሄድበት መንገድ ላይ ቆሞ መጠበቅ ጀመረ ።
ካልዳስ ሀገር ሰላም ብላ ጉዞዋን በምታደርግበት ሰዐት ድንገት ከበፊት ፍቅረኛዋ ጋር አይን ለ አይን ይገጣጠማሉ ። ክፉ ለማድረግ ያሰብው አፍቃሪም ወደ መኪናው በማስገደድ ያስገባታል ።
በመቀጠልም መኪናውን በፍጥነት እያሽከረከረ ወደቤቱ ይዟት በመሄድ አንድ አስከፊ ነገር ይፈጽማል ። በ 18 አመቷ ታያኔ ካልዳስ የፊት ገጽታ ላይ ሙሉ ስሙን ከ ቀኝ ጆሮዋ እስከ አገጭዋ ይነቅሳል ።
ይሄን ተግባር በፈጸመ በቀናት ውስጥ ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሎታል ።ካልዳስ ከ ጥቃቱ በኋላ ለ አንድ የ ሀገሬው ቴሌቭዥን በሰጠችው ቃል ባደረገው ድርጊት እጅግ አፍሬያለሁ ለሰራው ስራ የትንሽ ጊዜ እስር ቢፈረድበት ነው ነገር ግን ከዛ በኋላ ምንም ዋስትና የለኝም ለህይወቴ እፈራልሁ ብላለች ።
ብራዚላውያን በዚህ ዜና ክፉኛ ሲበሳጩ በሀገሪትዋ የሚገኙ የንቅሳት ማሶገጃ ባለሞያዎች ካልዳስን ለመርዳት ተረባርበዋል ። በአሁኑ ሰዐትም የመጀመሪያ ዙር የማጥፋት ሙከራ የተደረገላት ሲሆን በቀጣይ ቀናቶች ሙሉ ለሙሉ እንደሚጠፋ ተስፋ ሰጥተዋታል ። ፍርድ ቤትም ይሄን ድርጊት የፈጸመው ግለሰብ ላይ ፍርድ ለመስጠት የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል ።
በተለያዩ ምክንያቶች በሴት ልጆች ላይ የሚደረጉ አስከፊ ተግባሮች በብዙ የአለማችን ክፍሎች ሲፈጸሙ እንሰማለን ። በሀገራችንም በሚፈጠሩ አለመግባባቶች እንስቶች አሲድ እንደተደፋባቸው ያየነው የሰማነው አሳዛኝ ታሪክ ነው ።
ንዴት ለትንሽ ደቂቃ የምትቆይ ክፉ መንፈስ ናትና ለዘላለም ጸጸት የሚዳርግ ተግባር ከመፈጸማችን በፊት ቆም ብለን እናስብ መልዕክታችን ነው ።
በዮሴፍ ከበደ
2022-06-06
