የኢትዮጵያ የገንዘብ መደብ ብር በመሆኑ በብሔራዊ ባንክ በሌላ አኳኋን ካልተፈቀደ በስተቀር በሀገሪቱ የሚከናወኑ ማናቸውም የገንዘብ ግንኙነቶች ሁሉ የሚከፈሉት በብር እንደሚሆን የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 591/2000 በግልጽ እንደሚደነግግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም በክፍያ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 718/2003 መሠረት በየትኛውም የክፍያ መፈጸሚያ ሰነድም ሆነ ሥርዓት ያለ ብሔራዊ ባንክ ፍቃድ የገንዘብ ዝውውርም ሆነ ገንዘብ ነክ አገልግሎት መስጠት አይቻልም ሲል ያጠናክራል፡፡
ታዲያ አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ግብይት የሚፈጸምበት ዘዴ እንደመሆኑ እና የሉላዊነትን በር በመጠቀም በበርካታ ሀገራት ተግባራዊ እየሆነ ያለው ምናባዊ ንብረትን ወይንም ዲጂታል መገበያያ ገንዘብ በኢትጵያም ተግባራዊ መሆን መጀመሩን የብሄራዊ ባንክ መረጃ ያመላክታል፡፡
ባንኩ በጥናት አረጋግጫለሁ ባለው መሰረት በአሁኑ ወቅት ከህግ እውቅና ውጪ እንደ ቢትኮይን እና የመሳሰሉት የምናባዊ ንብረት (ዲጂታል መገበያያ ገንዘብ) አገልግሎት በኢትዮጵያ እየተስፋፋ መምጣቱን ተናግሯል፡፡
ሀገሬ ቴቪ በስልክ ያነጋገራቸው የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ አቶ ሰለሞን ደሰታ “በኢትዮጵያ ዲጂታል መገበያያ ገንዘብን የሚደግፍ ሕግ የለም፤ ገንዘብ የማተም እና የማሰራጨት ስልጣኑ የብሔራዊ ባንክ ነው፡፡ ባንኩ ከፈቀደው ውጪ ስራ ላይ ሊውል የሚችል ገንዘብ የለም ፡፡” ብለዋል፡፡
የዲጂታል መገበያያ ገንዘብ ለግብይት ወይም ለክፍያ መጠቀም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዕውቅና ያልተሰጠው ድርጊት በመሆኑ ሕብረተሰቡ ከእንደዚህ አይነት ሕገ-ወጥ ተግባር እራሱን እንዲጠብቅ ባንኩ አሳስቧል፡፡
ባንኩ በተጨማሪም ይህ ተግባር ከብሔራዊ ባንክ እውቅና ውጪ ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር የሚደረግበት እና በተለይም በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ለማሸሽ ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል ብሏል፡፡
ይህ እየተስተዋለ ያለው ምናባዊ ንብረትን (ዲጂታል መገበያያ ገንዘብን) ለግብይት ወይም ለክፍያ መጠቀም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዕውቅና ያልተሰጠው ድርጊት በመሆኑ ሕብረተሰቡ ከእንደዚህ አይነት ሕገ-ወጥ ተግባር እራሱን መጠበቅ ይኖርበታል፡፡
ምክትል ገዢው ሲጨምሩ “ወደ ፊት የክሪፕቶ ካረንሲ ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ ተግባራዊ ልታደርግ ትችል ይሆናል፤ እስከዚያው ግን ከብሔራዊ ባንክ እውቅና ውጪ በመሆኑ ሕብረተሰቡ ላይ ለሚመጣ መዘዝ ተጠያቂ አይደለንም፡፡ መጠንቀቅ ይገባል !!” ይላሉ፡፡
የዲጂታል መገበያያ ገንዘብ በሕገወጥም ሆነ በሕጋዊ መንገድ በዓለማችን 154 ሀገራት ላይ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ በአፍሪካ ኬንያ ፣ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ተጠቃሚዎች ተርታ ውስጥ ተበድበዋል፡፡
በፍሬህይወት ታደሰ
2022-06-06
