ሀገሬ ቲቪ

የአውሮፓ የክርስትና ማእከሏ ሉአላዊነት

ቫቲካን ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በአውሮፓ የክርስትና ማእከል በመሆን አገልግላለች። በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1929 በተደረገ ስምምነት ደግሞ ሉአላዊት ሃገር እንድትሆን ስምምነት ተደርጓል። ቫቲካን የ1.2 ቢሊዮን የካቶሊክ እምነት ተከታዮች መንፈሳዊ ቦታ እና የካቶሊክ ፖፕ መኖሪያ ከተማ ናት። ይህችው ከተማ ሉአላዊት እንድትሆን የሚፈቅደው ውል ተፈጻሚ እንዲሆን የተደረገው ከ93 አመታት በፊት በዛሬዋ እለት ነበር።

ለቫቲካን ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በቅዱስ ጴጥሮስ መቃብር ላይ ቤተ ክርስቲያን ከተገነባ ጀመሮ የካቶሊክ እምነት ማእከልነቷ ጅማሮ እንደሆነ ይነገራል። ለዘመናት የሃይማኖታዊ ጉዞ ማእከል ብሎም የካቶሊክ ፖፕ መቀመጫ ሆና ዘልቃለች። በተለያየ ጊዜም አስደማሚ የኪነ ህንጻ ውጤቶች በከተማዋ እንዲገነቡባት ሆኗል።

በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሮም ንጉስ የነበረው ኮንስታኒቲን ክርስትናን ከተቀበለ በኋላ በቅዱስ ጴጥሮስ መቃብር ላይ ቤተ ክርስቲያንን ማሳነጹ ከተማዋን ለክርስቲያን ተጓዦች ቅዱስ ቦታ ለቀሳውስት መኖሪያ እና የንግድ ማእከል እንድትሆን አድርጓታል። በቀጠናው የተደረጉ የተለያዩ ጦርነቶች መዘዝ ቢያርፍባትም ቫቲካን ማእከልነቷ እንደተጠበቀ እስከዚህ ዘመን ደርሳለች።

በ16ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ በፖፕ ጁሊየስ ሁለተኛ ከተማዋ ትልቅ ለውጥ አስተናግዳለች። ሚካኤልአንጀሎ የሲስቲን ቻፕል ጣሪያን እንዲያስውብ ተደረገ። የዘመኑ አርክቴክት ዶናቶ ብራማንቴ የሺህ ዘመን እድሜ ያለውን የቅዱስ ጴጥሮስን ህንጻ እንደገና እንዲገነባ ጳጳሱ ፍቃዳቸው ሆነ።

ከጳጳሱ ጁሊየስ ሁለተኛ ህልፈት በኋላ ፕሮጀክቱን የመቀጠሉ ሃሳብ የአስርት አመታት አለመግባባት አስከትሎ ነበር። ኋላም ሚካኤልአንጀሎ የብራማንቴ ዲዛይንን ለመከተል በመስማማቱ ሲሰራ ቆይቶ በማለፉ የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተክርስቲያን ስራ ቀጥሎ በ15ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ተጀመሮ በ16ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ተጠናቋል።

ቤተ ክርስቲያኑም በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ የአይቮሪኮስቱ ቤተክርስቲያን እስኪሰራ የአለም ትልቁ ቤተ ክርስቲያን ሆኖ ቆይቷል።ጳጳሳቱ ፓፓል በሚባሉት ግዛቶች ላይ ስልጣን የነበራቸው የተዋሃደች ጣሊያን መንግስት ከከተማዋ ቅጥር ውጭ ያለውን መሬት በአውሮፓውያኑ 1870 እስከወሰደ ድረስ ነበር። በዚሁ ምክንያት ስምምነት ላይ እስኪደረስም ለ60 አመታት ያክል በቤተክርስቲያኗና በመንግስት መካከል ፍጥጫ ሆኗል።

ኋላም በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ1929 መንግስት እና ቤተክርስቲያኗ ላተራን ፓክትስ የተሰኘ ስምምነትን ተፈራርመዋል። ቤኒቶ ሞሶሎኒ ንጉስ ቪክቶር ኢማኑኤል ሶስተኛን ወክሎ በተፈራረመው በዚህ ስምምነት ቫቲካን ሉአላዊት ግዛት እንድትሆን ተስማምተዋል።

ቫቲካን የርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ ብሎም የ1.2 ቢሊዮን የካቶሊክ ምእመናን መንፈሳዊ ማእከል ሆና ለዘመናት ቆይታለች። የአለማችን ትንሿ ነጻ ሃገር የ44 ሄክታር ስፋት አላት። የክፍለ ዘመናት እድሜ ያላቸው ህንጻዎች እና የአትክልት ቦታዎችን በውስጧ አቅፋ የራሷ የባንክ፣ የቴሌፎን፣ የፖስታ፣ የፋርማሲ፣ ጋዜጣ፣ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን ማእከላት አሏት። የጳጳሳቱን ደህንነት የሚጠብቁትን የስዊዝ ዜጎችን ጨምሮ 800 ያክል ሰዎች በከተማዋ ይኖሩባታል።

በአብርሃም በለጠ
2022-06-07