የጤና ሚኒስቴር የዝንጀሮ ፈንጣጣ፣ የወባ በሽታና ኮቪድ 19ን አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ባለፉት አስር ወራት ብቻ አንድ ነጥብ ሶስት ሚልየን ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውን አመልክተዋል።
መግለጫውን የሰጡት የ ጤና ሚኒስቴር ዴኤታው ዶክተር ደረጄ ዱጉማ የወባ ወረርሽኝ በይበልጥም በደቡብ ክልል ፤በአማራ፤በኦሮሚያ፤ እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በ አፋጣኝ እየጨመረ በመሆኑ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል ።
አህጉራችን አፍሪካ 75 በመቶ ለወባ ወረርሽኝ ምቹ ናት ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታው በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2021 ብቻ 14 ሚሊየን ሰዎች በበሽታው የተያዙ ሲሆን 90 በመቶው ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገሪት ውስጥ የተከሰተ ነው ብለዋል ።
የ ኮቪድ 19 ወረርሽኝን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫም ባሳለፍነው ሳምንት በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር የጨመረ ሲሆን 14 ሰዎች በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ እንደሚገኙ አመልክተዋል ።
ሚኒስቴር ዴኤታው ከሰሞኑ አነጋጋሪ እየሆነ ስለመጣው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ያነሱ ሲሆን በሽታው እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳልገባ አስታውቀው በሀያ የድንበር ኬላዎች ላይ ቁጥጥር እያደረግን ቢሆንም ህብረተሰቡ ጥንቃቄ አይለየው ብለዋል ።
በዮሴፍ ከበደ
2022-06-07
