ሀገሬ ቲቪ

የዚኽ ዓመት ዓለም አቀፍ የምጣኔሀብት ዕድገት ትንበያ

በሚቀጥሉት ዓመታት በምጣኔሀብቱ ረገድ ዓለም ጠንከር ያለ ፈተና እንደሚገጥማት የዓለም ባንክ ይፋ ባደረገው ትንበያ አስታውቋል።የዓለም ባንክ በጉዳዩ ላይ እንደተናገረው ከሆነ የተንቀራፈፈ ምጣኔሀብታዊ እድገት እና ከፍ ያለ ዓለም የዋጋ ግሽበት ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎቻችን ሊሆኑ ይችላሉ ብሏል።

በዚኽ ዓመት ዓለም የሚኖራት የምጣኔ ሀብት ዕድገት 2ነጥብ9 በመቶ ሊወርድ አሊያም ሊያሽቆለቁል እንደሚችል ነው የተነበየው። በአውሮፓውያኑ የጥር ወር ይኽው ግምት 4ነጥብ1 በመቶ ነበር።

የኮቪድ 19 ቫይረስ መከሰት በዓለም አቀፍ ደረጃ የምርት ማሽቆልቆልና የሀገራትን ምጣኔሀብት መድቀቅ አስከትሏል። በእንቅርት ላይ ጆሮደግፍ እንዲሉ በዚኽ መሰናክል ላይ ለብዙ ሀገራት የገቢ ንግድ ምንጭ የሆኑት ዩክሬን እና ሩሲያ ጦር መማዘዛቸው ደግሞ ችግሩን ጠንካራ እንደሚያደርገው ነው የዓለም ባንክ የተናገረው። የሁለቱ ሀገራት ጦርነት መግጠም የሸቀጦች ዋጋ ጣራ እንዲነካ አድርጓል።

በነዚኽ በተጠቀሱት ምክንያቶች ታዲያ በርካታ ሀገራት የምጣኔሀብታዊ ውድቀት እንደሚገጥማቸው ነው የተገለጸው። የዓለም ባንክ የተንቀራፈፈ ሲል የገለጸው የምጣኔሀብት ዕድገት ምን አልባትም አስር አመታትን ሊዘልቅ እንደሚችል ነው የተናገረው። እንደምክንያት የተቀመጠው ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታየው የኢንቨስትመን እንቅስቃሴ አጥጋቢ ባለመሆኑ ነው ተብሏል። የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ዴቪድ ማልፐስ እንደተናገሩት የተንቀራፈፈ ምጣኔሀብታዊ ዕድገት፣ ሥራ አጥነት እና የዋጋ ግሽበት ከፍተኛ ትኩረት ሊሠጣቸው ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

ባንኩ በአውሮፓውያኑ 2023 እና 2024 የዓለም ምጣኔሀብት ዕድገት 3በመቶ አካባቢ ሊያንዣብብ እንደሚችል እና በብዙ ሀገራት የዋጋ ግሽበት ከፍተኛ መኾኑን ተነግሯል።

በምጣኔሀብት ትንበያው አሜሪካ እና አውሮፓ የዚኽ ዓመት ዕድገታቸው 2ነጥብ 5 በመቶ ብቻ እንደሚሆን ተገልጿል። የአሜሪካ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ 5ነጥብ7 በመቶ የቀነሰ ይኾናል እንደማለት ነው።

ሌላዋ የጠነከረ ምጣኔ ሀብት አላት የምትባለው ቻይና የዚኽ ዓመት ዕድገቷ አምና ካስመዘገበችው 8 ነጥብ 1 በመቶ በመውረድ 4 ነጥብ 3በመቶ እንደሚኾን ነው የተተነበየው። ሀገሪቱ ኮቪድ 19 ምክንያት አድርጋ በሀገሪቱ የጣለችው የእንቅስቃሴ ገድብ ለዚኽ የቀነሰ ዕድገቱ መንስዔ ኾኖ ቀርቧል።

በሙሉጌታ በላይ
2022-06-08