ለብዙዎቻችን የምሬት ምክንያቶች ናቸው።
ከሳሎን ቤት የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች አንስቶ በየ ኮመዲናው፣ በምግብ ቤት ውስጥ ባሉ ካቢኔቶች ሁሉ መኖሪያቸው አድርገውት ይገኛሉ። በረሮዎች።
ቤቱ የነሱ እስኪመስል ድረስ እንዳሻቸው ለመፈንጨት ከልካይ ያለባቸውም አይመስሉ።
ታዲያ እነዚሁ ጉደኛ በረሮዎች ፍርድ ቤት ውስጥ ሰተት ብለው ችሎትን አውከዋል መባሉን ሰማን።
በዚህም ሳቢያ የእለቱ ችሎቶች ተሰርዘው የፍርድ ቤቱ ህንፃ ተዘግቶ ውሏል።
እጅግ የበዛ የንፅህና መጠበቂያ መንገዶችን በሚከተለው የኒውዮርክ ፍርድ ቤት በረሮዎቹ በገፍ እንዴት ሊገኙ ቻሉ?
ነገሩ ከዚህ ይጀምራል።
በኒውዮርክ ሰሜናዊ ግዛት አልባኒ ከተማ ፍርድ ቤት ውስጥ አራት ሰዎች በፖሊስ ተይዘው የፍርድ ሂደታቸው እየታየ ነበር።
በመሀል አንደናው ተከሳሽ የፍርዱን ሂደት መቅረፅ ይጀምራል።
ዳኛውም ድርጊቱን እንዲያቆም እና መደበናውን የፍርድ ሂደት እንዲከታተል ያዙታል።
ነገሩ በዚህ ብቻ አላበቃም በፍርድ ቤቱ አንባጓሮዎች መነሳት ጀመሩ፤ በመሀል ከየት እንደሆኑ አድራሻቸው የማይታወቁ በረሮዎች ፍርድ ቤቱን ሞሉት።
ከተፈጠረው ነገር በኋላ ፖሊስ ጉዳዩን እየመረመረው እንደሆነ አስታውቋል።
በረሮዎቹም ከውጪ በፕላስቲክ ከረጢት ተሸክፈው ወደ ፍርድ ቤቱ እንደገቡም ደርሼበታለውም ብሏል።
ታዲያ ለዚህ ሁሉ ምስቅልቅሎሽ የፍርድ ሂደቱን ሲታደሙ ከነበሩት መሀል አንዲት የ34 ዓመት ሴትን ፖሊስ ተጠያቂ አድርጓታል።
በፍርድ ቤቱ በተነሳው አምባጓሮ ፈጣሪነት፣ በስርዓት አልበኝነት፣ የአስተዳደር ስራን በማወክ እና ማስረጃዎችን በማበላሸት ክስ እመሰርትባታለው ብሏል ፖሊስ።
የፍርድ ቤት አስተዳደር ፅህፈት ቤት እንዳለው ከሆነ የተፈጠረው ነገር የተጠርታሪዎቹን ንፅሕና ለሳየት ወይም አክቲቪዝም ሳይሆን የፍርድ ሂደቱን ለማወክ እና ጉዳት ለማድረስ በማሰብ የተደረገ ወንጀል ነው።
ከዚህ ሁሉ በኋላ ታዲያ በፍርድ ቤቱ ሲርመሰመሱ የነበሩ በረሮዎችን ለማጥፋት፤ ፍርድ ቤቱ በጢስ እንዲታፈን ተደርጎ ተዘግቶ ውሏል።
በሳምሶን ገድሉ
2022-06-08
