በሁሉም ወገኖች ለሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂነት እንዲኖር የአሜሪካ ኤምባሲ በኢትዮጵያ ጠየቀ፡፡ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ያሉ አስፈላጊ አገልግሎቶች በአስቸኳይ እንዲመለሱ እና ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰላም እንዲሰፍን ብሎም ግጭቶች እንዲቆሙ ሲል የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አመላክቷል፡፡
ባለፉት ሰባት ቀናት ውስጥ ከ1 ሺሕ 100 በላይ የጭነት መኪናዎች ትግራይ ገብተው ህይወት አድንና የተመጣጠኑ ምግቦች፣ ህክምና፣ የጤና አቅርቦቶችን እና ሌሎች አስፈላጊ የእርዳታ ቁሳቁሶችን ለችግር ተጋላጭ ለሆኑት እንዲደርስ ሁሉም የሰብአዊ እርዳታ ሰጭ አካላት ላደረጉት ርብርብ ምስጋና ሰጥቷል፡፡
የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ጄ ብሊንከን በአፋር፣ በአማራ እና በትግራይ የኢትዮጵያ ክልሎች ለተቸገሩ ማህበረሰቦች ተጨማሪ መደበኛ የሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲያገኙ በማድረግ ላይ ያለውን መሻሻል አድንቀዋል፡፡በተለይም የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የአፋር ክልል ባለስልጣናት እና የትግራይ ክልል ባለስልጣናት ይህን እርዳታ ለማድረስ የሚያደርጉትን ትብብር እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የአሜሪካ መንግሥት አጋሮች እና ግብረሰናይ ድርጅቶች በመላው ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጥረት እናደንቃለን ብለዋል፡፡
በፍሬህይወት ታደሰ
2022-06-08
