ለሰው ልጅ የውበት መለኪያ ተዘጋጅቶ ቁንጅና ይመዘንበት ዘንድ በርካታ ውድድሮች ይደረጋሉ። ለእንስሳትስ የቁንጅና ውድድር ስለመኖሩ ቢሰሙስ? በሳውዲ አረቢያ ከ40 በላይ ግመሎች ከቁንጅና ውድድር ውጭ መደረጋቸውን ሰማንና ተደነቅን። እነዚህ ከአርባ የሚልቁት ግመሎች ያልተፈቀደ መዋቢያ (ኮስሞቲክስ) ተጠቅመው በመገኘታቸው ነው ከውድድሩ ውጭ የተደረጉት። ውድድሩ የንጉስ አብዱላዚዝ የግመል ፌስቲቫል አንዱ ድምቀት እንደሆነም ይነገርለታል። ርዝመት፣ የተንጠለጠሉ ከንፈሮች፣ ትልቅ አፍንጫ እና የተዋበ ቅርጽ ያለው ማጅራት (ጉብታ) ለግመሎቹ የውበት መለኪያዎች ሆነው ቀርበዋል። ውብ ሆኖ የተገኘ ግመል 66 ሚሊዮን ዶላር አልያም ከሦስት ቢሊየን በላይ የኢትዮጵያ ብርን የግሉ ያደርጋል። የቦቶክስ መርፌ እና ሌሎች የመዋቢያ ኮስሞቲክሶችን ተጠቅመው የተገኙት አነዚህ ከውድድር ውጭ የሆኑት ግመሎች ውድድሩን አደጋ ላይ ጥለውታል ነው የተባለው። ግመሎቹ የወሰዱት ቦቶክስ የቆዳ መሸብሸብ እንዲቀንስ እና ውበትን እንዲጨምር የሚረዳ መድሃኒት ነው። 27ቱ ተወዳዳሪዎች ያልተስተካከለ የሰውነት ቅርጽ በመያዛቸው ከውድድሩ ውጪ ሲሆኑ 16 ቱ ደግሞ ውበታቸውን ለማጉላት መርፌ ተጠቅመው በመገኘታቸው ከውድድሩ ውጪ ሆነዋል ሲል የሳዑዲ ፕሬስ ኤጀንሲ ጽፏል። ታዲያ ይህንን ማለታችን በዛሬው ዕለት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የእንስሳት መብት ቀን ተብሎ ስለሚከበር ነው። እንደ አውሮፓውያኑ በ1970 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንስሳት እራሳቸውን መጠበቅ ስለማይችሉ ብቻ የሚደርስባቸው ስቃይ ይበቃል ሲል ቀኑን ለነጻነታቸው መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ሰይሞታል። እንስሳት የሰውን ፍላጎት ለማሟላት ብቻ ነው የተፈጠሩት የሚለው አስተሳሰብ ምክንያታዊ ያልሆነ ጭፍን ጥላቻ ነውና ልናስወግደው ይገባል ሲል ነው ቀኑን የሰየመው።
በሀገሬ ቲቪ
2021-12-10
