የአዲስ አበባ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ቀልጣፋ ተደራሽእና ፍትሃዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል በሚል ከነሐሴ 24 /2011 ጀምሮ የኤሌክትሮኒክስ ታክሲ ስምሪት መመሪያ ተግባራዊ ማድረጉ አይዘነጋም።
ይሁን እንጂ ይህንን መመሪያ በመጣስ በሕገወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የሜትርና የኤሌክትሮኒክስ ታክሲዎች በመኖራቸው
እንደ አዲስ ለመመዝገብ መገደዱን ቢሮው አስታውቋል፡፡
የሜትርና የኤሌክትሮኒክ ታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ማኅበራትና ድርጅቶችን ለመቆጣጠር በሚያስችል መንገድ ማሻሻያ መደረጉንም ከሪፖርተር ሰምተናል፡፡
በዚህ መሠረት አገልግሎት ሰጪዎቹን እንደ አዲስ መመዝገብ ማስፈለጉን፣ በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የሕዝብና ጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የስምሪት ዳይሬክተር አቶ አልዓዛር ይርዳው ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ 53 የሜትር ታክሲ ማኅበራት መኖራቸውን ገልጸው በእነዚህ ማኅበራት ውስጥም 2ሺሕ 800 ተሽከርካሪዎች ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ከእነዚህ ውስጥም ፈቃዳቸውን በወቅቱ ያላደሱ በርካታ ማኅበራት በመኖራቸው ለቁጥጥር እንዲያመች ቢሮው በድጋሚ ምዝገባ ለማድረግ ተገዷል፡፡
በተጨማሪም እስካሁን በቢሮው ዕውቅና ያገኙት የኤሌክትሮኒክ ታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች 17 ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውጪ ያለፈቃድ የሚሠሩ መኖራቸውን ተደርሶበታል፡፡
በፍሬህይወት ታደሰ
2022-06-08
