ወደ ባንኮክ እናምራ በዚህች ከተማ ነዋሪነቱን ያደረገ የያኔው ወጣት የፋርማሲ ባለሙያ የዛሬው በጡረታ የተገለሉ የ73 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ እናውጋችሁ፡፡
እኚህ ሰው የሰሞኑን የብዙሃን መገናኛ የፊት ገጽ በመሆን ዓለምን አነጋግረዋል፡፡ ብዙ ለፍቅር መስዋትነት የከፈሉ ሰዎችን ታውቁ ይሆናል፡፡ የኚህ አዛውንት የፍቅር ህይወት ግን እኛን በእጅጉ አስገርሞን ልናጋራችሁ ወደድን ፡፡
ቻርን ጃንዋካል ከፍቅር አጋራቸው ጋር የተዋወቁት እርሳቸው በፋርማሲ የትምህርት ክፍል ተመርቀው በሮያል ታይ ጦር ውስጥ የሕክምና ባለሙያ ሆነው በተቀጠሩ ማግስት ባለቤታቸው በዚያው ሆስፒታል የፋርማሲ ባለሞያው ሆነው ይሰሩ እንደነበር ያወጋሉ ፤ እጅግ ውብ ፣ዝምተኛ እና ደግ ሴት እንደነበሩ በማስታወስ ፡፡
“የመጀመሪያ ዲግሪዬን ከፋርማሲ የትምህርት ክፍል እንደጨረስኩ ታይ ጦር ውስጥ በመቀላቀል ስራ ጀመርኩ እርሷ ደግሞ በዚያው ሆስፒታል ውስጥ የፋርማሲ ባለሙያ ነበረች በትህትናዋ ተማረኩ ገና ግንኙነት ሳንጀምር ተሸነፍኩላት በጣም ቆንጆ ነበረች፡፡ በጣም ደግ፣ ዝምተኛ እና የተረጋጋች ሴት ነበረች፡፡”
በትውስታ ወደ ኋላ እየተመለሱ ያንን ጣፋጭ የፍቅር ጊዜያቸውን ያስታውሳሉ የሆነው ሆነና የተመኙት ፍቅር እንዲያው አልቀረም ተጋቡና 2 ልጆችን ወለዱ ረዥም ዘመናትን በፍቅር ከኖሩ በኋላ ሞት አይቀሬ ነውና ባለቤታቸውን በሞት ያጣሉ።
ከዚህ በኋላ ነው እንግዲ ጉዱ የዛሬው ባለታሪካችን ቻርን ጃንዋካል ባለቤታቸውን አላስቀብር ብለው የቀብር ስርዓቱን ያስታጉላሉ፡፡ ቀብርተኛውም አይ ግዴለም አላመኑም ሲቆይ ያምናሉ በሚል ይተዋቸዋል እኚህ ሰው ግን ባለቤታቸው እንዳልሞቱ በማመን አብረው እየኖሩ ነው፡፡
የባለቤታቸውን ህልፈት ተከትሎ አስክሬኑ እንዲቀበር ፍቃደኛ ባለመሆናሸው ልጆቻቸው በአባታቸው ወሳኔ ከቤት ለመውጣት ተገደዋል።
እርሳቸው ግን 21 ዓመታትን ሙሉ የባለቤታቸውን አስክሬን ታቅፈው በቤታቸው ኖረዋል፡፡
የባለቤታቸውን አስከሬን ከሚተኙበት ጎን በሚገኝ ትንሽ ክፍል ውስጥ አስቀምጠው በህይወት እንዳሉ በማስመሰል እያነጋገሯቸው ኖረዋል፡፡
ታዲያ ከዚህ ሁላ ዓመት በኋላ የሞተር ሳይክል አደጋ ይደርስባቸው እና ተንከባካቢ በመሻታቸው ፌት ካሰም ባንኮክ ፋውንዴሽን እርዳታ ድርጅት ወደ ጊቢያቸው ይዘልቃል ፤ለሁለት ወራት ያክል እንክብካቤ ሲደረግላቸው በቤቱ ውስጥ ያለውን የሬሳ ሳጥኑ በማስተዋል ይመለክታሉ ከዚያማ ከ21 ዓመታት በኋላ በፌት ካሰም ባንኮክ ፋውንዴሽን እርዳታ በማግኘት አሳምነዋቸው የሚስታቸውን አስክሬን ለማቃጠል በመገደዳቸው በዚሁ ዓመት በሚያዚያ መጨረሻ አስክሬኑ እንዲቃጠል ተወስኗል፡፡
በማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ በተሰራጨው የአስከሬን ቃጠሎውን የተመለከቱ ምስሎች የሚያሳየው በፋውንዴሽኑ ሰራተኞች እየተረዱ የባለቤታቸውን የሬሳ ሳጥን በዋና ከተማው ባንኮክ ባንግ ኬን አውራጃ ከቤታቸው ይዘው ወጡ፡፡
ይሁን እንጂ እኚህ የ73 ዓመት አዛውንት አሁንም ባለቤታቸው እንደሞቱ አያስቡም ትመጣለች ከሄደችበት እያሉ ሲያወሩም ተሰምተዋል፡፡
“እማዬ፣ ለአጭር ጊዜ ለሆነች ጉዳይ ነው ምትሄጂው ወደ ቤት ትመለሻለሽ ብዙም አትቆይም ቃል እገባልሻለሁ።”
አንዳንዶች ይህ ፍቅር እስከ መቃብር ብቻ ሳይሆን ከመቃብር በላይ ነው በማለት ነገሩን አድንቀውታል፡፡ የእኚህ አዛውንት የፍቅር ህይወት ለብዙዎች የፍቅርን ዋጋ ማሳያ በሚል ሲሰራጭ ከርሟል፡፡
በፍሬህይወት ታደሰ
2022-06-09
