ሀገሬ ቲቪ

የፓስፖርት ክፍያን በቴሌብር መክፈል የሚቻልበት አሠራር ይፋ መኾን

ኢትዮቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራሁ ነው ብሏል። ዛሬም ታዲያ ከአገልግሎት ዘርፉ አንዱ ከሆነው ከኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ጋር በጋራ በመሆን ዜጎች ለክፍያ ወደ ተቋሙ መሔድ ሳይጠበቅባቸው አዲስ ፓስፖርት ማውጣት፣ ማደስ፣ ለጠፋ ምትክ ማውጣት የሚቻልበትን አሠራር ይፋ አድርጓል።

አዱሱ አሠራር ደንበኞች የቴሌብርን የዲጂታል የክፍያ ሥርዓት በመጠቀም የፓስፖርት ክፍያቸውን መፈጸም ይችላሉ።

ኢትዮቴሌኮም የአገልግሎት ዘርፉ እጅግ የቀለለ እንዲሆን ከተለያዩ የመንግሥት እና የግል ተቋማት ጋር አገልግሎትን ዲጂታላይዝ የማድረግ ሥራ እየሠራ ሲኾን ፓስፖርትን የተመለከቱ ክፍያዎች በቴሌ ብር ከመክፈል በተጨማሪ ደንበኞች ፓስፖርታቸው ደኽንነቱ ተጠብቆ ቤታቸው ድረስ የሚቀርብበት አሠራር ለመዘርጋት በሒደት ላይ እንደሆነ የኢትዮቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ት ፍሬሕይወት ታምሩ ተናግረዋል።

አዲሱ የክፍያ ዘዴ የቴሌኮም አገልግሎትን በቀላሉ በመጠቀም አገልግሎቱን ከማዘመን ባለፈ ከፓስፖርት ክፍያ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ተግዳሮቶችን እንደሚፈታ የኢግሚሬሽንና እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ብሩህተስፋ ሙሉጌታ ገልጸዋል።

ኢትዮቴሌኮም ከአንድ ዓመት በፊት ተግባራዊ ያደረገው ቴሌብር የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት አሁን ላይ 20 ሚሊዮን ደንበኞች ሲኖሩት 20.6 ቢሊዮን ብር ግብይት ተከናውኖበታል።

በሙሉጌታ በላይ
2022-06-09