ከተቀሰቀሰ ወራትን ያስቆጠረው የሩሲያና የ ዩክሬን ቀውስ ዳፋው በሁለቱ ሃገሮች ብቻ ሳይገደብ መላ አለምን አዳርስዋል ። በይበልጥም የጦርነቱ ገፈት ቀማሽ የሆነችው አህጉራችን አፍሪካ ናት ። በምግብ እጦት በ ኑሮ ውድነት በህዝቦች መሰደድ ሌላም ሌላም ።
በዩክሬንና ሩሲያ መካከል ቀድሞውንም ቀውስ ሊያስነሱ የሚችሉ ድምጾች ሲሰሙ በ ምጣኔ ሀብት ባለሞያች ዘንድ ተው ይህ ጦርነት የዓለምን ኢኮኖሚ ያሽመደምዳል፣ የምግብ እጥረት ይፈጠራል፣ታይቶ የማይታወቅ የዋጋ ግሽበት ይከሰታል በማለት ድምጻቸውን አሰምተዋል ። ነገር ግን ሰሚ ጠፋ ።
ባለሞያዎቹ ያሏት ቃል አልቀረችም ዓለም ከ 3 አስርት አመታት ወዲህ አስተናግዳ የማታውቀው የኑሮ ውድነት እንዲሁም የምግብ አቅርቦት እጥረት ተከሰተ ።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ከሌሎች ሀገራት የበለጠ አህጉራችን አፍሪካ ላይ የምግብ ቀውስ እንደደቀነ በዘገባው አመልክትዋል ።
ዩክሬን በየዓመቱ ለአፍሪካ 40 በመቶ ያህል ስንዴና በቆሎ የምትልክ ሲሆን ሩሲያ በበኩሏ ከ2018 እስከ 2020 ባለው ጊዜ አፍሪካ ከሚያስፈልጋት የስንዴ ምርት 32 በመቶ ያህሉን ትሸፍናለች፡፡
ታዲያ በየዓመቱ በቋሚነት የግብርና ግብዓቶች ስታስገባ የከረመችው አህጉራችን አፍሪካ ሁለቱ ሃገራት በጀመሩት ጦርነት ባልተጠበቀ የአየር ንብረት ቀውስ ድርቅና የእርስ በርስ ግጭት ምክንያት ዛሬ ላይ ለከፍተኛ የምግብ ቀውስ ተጋልጣለች፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ማብቂያ የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ወደ ሩሲያ አቅንተው፣ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በምግብ ዋስትና ዙሪያ መክረዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ፑቲን፣ ጦርነቱ እና በሩሲያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች ደካማ ኢኮኖሚ ያላቸው አገሮች ላይ የፈጠረውን ችግር እረዳለው ሲሉ
ከአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ጋር ባደረጉት ቆይታ ላይ የገለጹ ሲሆን ነገር ግን ምዕራባውያን ሞስኮ ከዩክሬን እህል እንዳይላክ አግዳለች ማለታቸው መሰረተ ቢስ የሆነ ውንጀላ ነው ሲሉ ኮንነዋል ።
ለሦስት ሰዓታት ያህል ከአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ጋር ውይይት ያደረጉት ቭላድሚር ፑቲን፣ “ሩሲያ ሁሌም ከአፍሪካ ወገን ናት ፤ በአፍሪካ ላይ ከማንኛውም ምግብ ፣ እህልና ጥራጥሬ እንዲሁም ማዳበሪያ ጋር የተያያዘ ማዕቀብ የለም” ብለዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ሳል በዩክሬንና ሩሲያ መካከል ባለው ጦርነት የምግብ እጥረት መከሰቱን በመግለጽ አገሮች ምግብና ማዳበሪያ ላይ ማዕቀብ እንዳይጣል እንዲያረጋግጡ የጠየቁ ሲሆን ፑቲን በበኩላቸው፣ ለዚህ ሁሉ ቀውስ ምዕራባውያንን ወቅሰው፣ ሩሲያ ከዩክሬን ለሚላኩ ምግቦች ደኅንነቱ የተጠበቀ መንገድ እንደምትከፍት ጠቁመዋል፡፡
ሰላማዊ´ መንገድ እናመቻቻለን፡፡ ከወደቦቹ ምግብ ጭነው ለሚሄዱና ከውጭ ለሚገቡ መርከቦች የእንቅስቃሴ ደኅንነት ዋስትና እንሰጣለን ሲሉም ቃል ገብተዋል፡፡
በዮሴፍ ከበደ
2022-06-10
