የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በከፍተኛ ድርቅ እና የምግብ ዕጥረት ምክንያት ፈተና ውስጥ ከገቡ ሰነባብተዋል።
ለአራት ተከታታይ ወቅቶች መዝነብ የነበረበት ዝናብ ባለመዝነቡ የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት በኢትዮጵያን ኬኒያ፣ እና ሶማሊያ ሊከሰት እንደሚችል ጠቁመው ነበር።
እንደተሰጋውም በቀጠናው ያጋጠመው የዝናብ ዕጥረት በሰብሎች ላይ እና በቁም እንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማደረስ ረሀብ እንዲከሰት ምክንያት ኾኗል።
ከሳምንት በፊት የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው መግለጫ በሶማሊያ ከ 2ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለከፍተኛ የምግብ ዕጥረት ተጋልጠዋል ብሏል።
በሶማሊያ የተከሰተው ድርቅ ከ 80 በመቶ በላይ ሀገሪቷን ጎድቷታል።
በተጨማሪ ድርቁ ሕጻናትን ከእናቶቻቸው እየነጠለ እንደሆነ ኤፍፒሲ የተሰኘው የዜና ምንጭ በሀገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር የሠራው ዘገባ ይገልጻል።
አርባይ ማሃድ ቃሲም የተባልች እናት ሁለት ሕጻናት ልጆቿ ረሀብ መቋቋም አቅቷቸው እንደሞቱባት ተናግራለች።
አኹን ላይ በጠና ታማ ሆስቲታል የገባችው ሦስተኛ ልጇ እንዳትለያት በሥጋት ላይ መኾኗንም ገልጻለች።
በርካታ እናቶች ኾኑ ቤተሰቦች የልጆቻቸው ዕጣ ፈንታ በጽኑ የሚያሳስባቸው ጉዳይ ኾኗል።
አንዳንዶች ዕርዳታ ለማግኘት በምግብ እጦት ሰውነታቸው የመነመኑ ሕጻናትን በጀርባቸው አዝለው ለቀናት በእግራቸው ተጉዘዋል።
እንዲኽ የጠነከረ ድርቅ ገጥሞን አያውቅም ያሉት የጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ዜጎች የተማጽዕኖ ጥሪያቸውን አሰምተዋል።
ከወራት በፊት ቢቢሲ በሰራው ዘገባ በሶማሊያ የተከሰተው ድረቅ በዚኹ የሚቀጥል ከኾነ በሀገሪቱ ካሉ 1ነጥብ4 ሚሊዮን ሕጻናት ውስጥ 3መቶ 50 ሺህ የሚሆኑት መጨረሻቸው ሞት ሊሆን እንደሚችል አስታውቋል።
70% እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናት በድርቁ ሳቢያ ትምህርታቸውን አይከታተሉም።
በጁባ ምድር በአንድ ግዛት ብቻ ድርቁ 40 ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ምክንያ እንደኾነ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ተናግሯል።
በሀገሪቱ ያሉ የጤና ባለሙያዎች በበኩላቸው ሆስፒታሎች አሁን ላይ በምግብ ዕጥረት የተጎዱ ሕጻናት እና አዋቂዎች መቀበል የምይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል ብለዋል።
ከሶማሊያ ባሻገር በቀጠናው በሚገኙ ሀገራት በአጠቃላይ 16 ሚሊዮን የሚጠቁት ዜጎች አፋጣኝ የምግብ ዕርዳታ ይሻሉ።
ከ 5 እስከ 6ነጥብ6 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች በኢትዮጵያ 3.5 ሚሊዮን በኬኒያ እና 6 ሚሊዮን በሶማሊያ ለከፋ የምግብ ዕጥረት መጋለጣቸውን ኢጋድ አስታውቋል።
በትላንትናው እለት ታዲያ የዓለም ባንክ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለኬኒያ እና ሶማሊያ 385 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አጽድቋል።
ድጋፉ ሀገራቱ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርስባቸውን ጉዳት ለመቋቋም የሚያስችላቸውን ፐሮጀክት ለመሥራት የሚረዳቸው ነውም ተብሏል።
በሙሉጌታ በላይ
2022-06-10
