ሀገሬ ቲቪ

15 ዓመት የተፈረደበት ጎብኚ

በብዙ መልኩ ኢራቅ የሰው ልጅ ሁሉ ታሪክ የያዘች ናት ቢባል ማጋነን አይሆንም። የኢራቅ ሙዚየም ግዙፍ ስብስብ የሰው ልጅን የስልጣኔ ታሪክ፣ ከቀደምቶቹ ሰፈራዎች እስከ ሰፊው ግዛት እድገት እና ውድቀት ድረስ ይተርካል።

እነዚህ ቅርሶች፣ አንዳንዶቹ ከ10 ሺሕ ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ፣ ከአደን እና ከጽሕፈት መሣሪያዎች እስከ ሂሳብ ጥበብ፣ ሕግ፣ ሃይማኖት እና ኢንዱስሪ ምኑ ተነግሮ ምኑ ይቀራል በርካታ ጥንታዊ እውቀቶችን የያዘች ጥንታዊ ሀገር ናት።

ይህንን ተከትሎ በርካታ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ወደ ሀገሪቷ ይተማሉ፤ከእነዚህ ጎብኚዎች መካከል የሆነው እንግሊዛዊ ጂኦሎጂስት ወደ ኢራቋ ባግዳድ ለጉብኝት እንደመጣ ሰማን።

ታዲያ ይህ እንግሊዛዊ ጎብኚ ከተማዋን እየተንሸራሸረ ሲያይ በኢራቅ የሚገኙ ጥንታዊ እና ታሪካዊ ስፍራዎችን ጎብኝቶ እንዳበቃ ወደ ሀገሩ መመለሱ ግድ ይሆንና መጋቢት 20 በባግዳድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ሀገሩ ለመግባት ሻንጣውን ሸክፎ ሊወጣ ሲል ቁም መንቀሳቀስ አትችልም ይባላል።

ጂም ፊቶን የጉምሩክ ባለስልጣናት በተገኙበት ሻንጣው ሲፈተሸ 12 ቁርጥራጮች ይዟል፤ወዲያው በፖሊስ ቁጥጥር ስር በመዋል ለፍርድ ቤት እንደቀረበ የሲኤንኤ መረጃ ያሳያል።

የፍርድ ቤቱ ክስ እንደሚያሳየው የ66 ዓመቱ እንግሊዛዊ ፊቶን ኢራቅ ውስጥ በሀገሪቱ በአርኪኦሎጂ ጉብኝት ላይ በነበረበት ወቅት የጥንት ቅርሶችን በመስረቅ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የ15 ዓመት እስራት እንደተፈረደበት ጠበቃውን ዋቢ በማድረግ ብዙሃን መገናኛ ዘግበዋል።

በዚህ ዜና የተደናገጡት ቤተሰቦቹ 12ቱን ቁርጥራጮች ሲያነሳ በኢራቅ ደቡባዊ ጥንታዊቷ ኤሪዱ የጂኦሎጂ እና የአርኪኦሎጂ ጉብኝት ላይ እንደነበር አልደበቁም ግን ዕቃውን እንዳይነሳ የሚከለክል ጠባቂም ሆነ ምልክት የለም ሲሉ ይከራከራሉ።

ጠበቃው በበኩሉ “ደንበኛዬ 15 ዓመት እስራት ተፈርዶበታል። እርሱ ቅርሶቹ ምን እንደሆኑ እንኳ በወጉ አያውቅም፤ በአርኪኦሎጂ አካባቢ ከቆሻሻ መጣያ የተወሰዱ መሆናቸውን ነግሮኛል ፤ምንም አይነት የወንጀል ዓላማ የለውም ድንጋይ እንደሚወድና ከጎበኘው ቦታ ሁሉ እንደሚሰበስብ አውቃለሁ፡፡” ብለዋል።

በተያዘው ሳምንት ሰኞ ብይን የተሰጠበት ፊቶን ቤተሰቦች ጡረተኛው ጂኦሎጂስት የእስር ጊዜውን ሳይጨርስ ሊሞት ይችላል ብለው እንደሚሰጉ ተናግረዋል።

ተባባሪ በሚል በእስር የነበረው ጀርመናዊው ወር ቮልከር ዋልድማን በማስረጃ እጦት ምክንያት ጥፋተኛ አለመሆኑ ተረጋግጦለታል። ተስፋ ያልቆረጡት ቤተሰቦች ለሲኤንኤን እንደተናገሩት “በዚህ ዜና ፍፁም ልባችን ተሰብሯል ብለዋል።”

“በፊቶን እድሜ ላለ ሰው በኢራቅ እስር ቤት 15 ዓመታትን መቆየት ከሞት ፍርድ አይተናነስም፤ በተለይ ለእንዲህ ዓይነቱ ቀላል እና አጠራጣሪ ወንጀል ሲፈጽም እንኳን ላላወቀው ወንጀል ይህን ያህል ዓመት አይገባውም።”

“በእኛ መንግሥት እስካሁን በዚህ ጉዳይ ላይ ባደረገው አጠቃላይ እርምጃ በጣም አዝነናል፣ በእርግጥም ደንግጠናል።" "ይግባኝ እያቀረብን ነው እናም ለጂም ነፃነት ትግላችንን እንቀጥላለን፣ መንግሥት በሚቻለው መንገድ ሁሉ እንዲደግፈን እና በከፍተኛ ደረጃ ከእኛ ጋር የግንኙነት መስመሮችን እንዲከፍት እናሳስባለን።”

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ልማት ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው “በኢራቅ ለሚኖረው እንግሊዛዊ ዜጋ የቆንጽላ እርዳታ እየሰጠን ነው፣እና ቤተሰቡን መደገፍ እንቀጥላለን፤ከአካባቢው ባለስልጣናት ጋር እየተገናኘን ነው።” ብለዋል።

ይህ ነግ በኔ ነው!! የፈረንሳይ፣የእንግሊዝ ፣የጀርመን እና የሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት ሙዚየሞች በማን ጥንታዊ ቅርሶች እንደተጨናነቁ መገመት አይከብድም የሚመጡ ጎብኚዎችን በጥንቃቄ ማየቱ አይከፋምና የኢራቅ ፍርድ ቤት ይበል ብለናል።

በፍሬህይወት ታደሰ
2022-06-10