ሀገሬ ቲቪ

እለቱን ከታሪክ - የህንድ ጠቅላይ ሚኒስተር የነበሩት የዮጋ መምህር

የዮጋ የአካል እና አእምሮ እንቅስቃሴ አሁን ላይ በዘመናዊው አለም ቅቡልነትን እያተረፈ ያለ ተግባር ነው። የህንድ ጠቅላይ ሚኒስተር የነበሩት የኢንዲራ ጋንዲ የዮጋ መምህር ይሄንን በምስራቁ አለም የሺህ አመታት እድሜ ያለውን ጥበብ ለሌላው አለም እንዲተዋወቅ በር ከከፈቱት መካከል ይጠቀሳሉ።

ድሂሬንድራ ብራህማቻሪ ይባላሉ። እኒህ ሰው የሶቭየት ህብረት ጠፈርተኞችን እንዲያሰለጥኑም በዮጋ ባለሙያነት ለመጋበዝ ችለዋል። ብራህማቻሪ ያረፉት በዛሬው እለት በ1986 ነበር።

በዘመናዊው አለም ዮጋ የተሰኘው የአእምሮ እና የአካል እንቅስቃሴ ለጤናማ አእምሮ እና አካል የሚመከር ተግባር ከሆነ ሰነባብቷል። ይሄው ጥንታዊ ተግባር ከምስራቁ የኤስያ ክፍል ወደ ሌላው የአለም ክፍል የመስፋፋት ጅማሮው በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ጀምሮ እንደሆነ ይነገራል።

በ20ኛው ክፍለ ዘመን ይሄንንው የዮጋ ጥበብ ለምእራቡ አለም እንዲተዋወቅ በር ከከፈቱት መካከል የሆኑት ብራህማቻሪበአሜሪካ ካሊፎርኒያ ተጀምሮ ለግማሽ ክፍለ ዘመን መዝለቅ የቻለውን እና ዮጋ በምእራቡ አለም የበለጠ እውቅና እንዲኖረው አስተዋጽኦ ያደረገውን 3HO የተሰኘ የዮጋ ትምህርት ቤትን እንዲመሰረት ያደረጉት የዮጊ ብሃጃን መምህርም ናቸው።

በ1916 ህንድ የተወለዱት ብራህማቻሪ መንፈሳዊ መጽህፍትን በማንበብ በመነሳሳታቸው በ13 አመታቸው ነበር ጥንታዊ የአካባቢውን ብልሃት ለመቅሰም ወደ ቫራናሲ የተጓዙት።

ዮጋ እና ተያያዥ ትምህርቶችንም ከአካባቢው መምህራን መቅሰም ችለዋል። ተር የነበሩትን የኢንዲራ ጋንዲን ጤናን ለማሻሻል የዮጋ መምህራቸው ሆነዋል።

የጠቅላይ ሚኒስተሯ መምህር መሆን የቻሉት ብራህማቻሪ በ1970ዎቹ በመንግስት የቴሌቪዥን ሚዲያ ላይ በሳምንታዊ ፕሮግራም የዮጋ ጥቅሙን የበለጠ ማስተዋወቅን ተያያዙት።

በህንድ ዋና ከተማ ደልሂ ባሉ ትምህርት ቤቶችም ዮጋን እንደ አንድ የትምህርት አይነት አስተዋውቀዋል። በመንፈሳዊ ተቋማት ውስጥ ይሰጥ የነበረውን ጥንታዊው ዮጋን በዘመናዊ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት ማድረጋቸው እንደ ትልቅ ፈጠራ ይታይላቸዋል።

በህንድ የዮጋ ብሄራዊ ኢንስቲትዩት እንዲከፈት ከማድረጋቸውም በተጨማሪ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ደረጃ ዮጋ እንዲሰጥ አድርገዋል።በተጨማሪም የእነዚህ ተቋማት ባለቤትም ነበሩ።

ዮጋን ለማስተዋወቅም መጽህፍትን በሂንዱ ከመጻፋቸው በተጨማሪም ለሌላው አለም ማህበረሰብም ለማስተዋወቅ በእንግሊዘኛ መጻህፍትን ጽፈዋል። በተጨማሪም ፈለጋቸውን የሚያስቀጥሉ ተከታዮችን ማፍራትም ችለዋል።

የዮጋ ጥበብን በማስተዋወቅ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማሳረፍ የቻሉት ብራህማቻሪ ያረፉት በ70 አመታቸው በዛሬው እለት ከ28 አመታት በፊት ነበር።

በአብርሃም በለጠ
2022-06-10