የስኳር ህመም በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም ላይ እየተስፋፋ ያለ ህመም ሲሆን የሥርጭቱ መጠንም ወረርሽኝ ወደ ሚያስብለው ደረጀ ደርሷል።
በኢትዮጵያ የስኳር ህመም ከዛሬ 3ዐ ዓመታት በፊት አልፎ አልፎ ብቻ ሲታይ የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በሚያስደነግጥ መልኩ እየተስፋፋ ለመሆኑ ወደ ጤና ድርጅቶች ለህክምና በሚመጡት ስዎች ቁጥር ብዛት ለመረዳት ይቻላል።
የስኳር ህመም የሚከሰተው ሰውነታችን ለኑሮም ሆነ ለእድገት የሚያስፈልገውን ስኳር በትክክል ለመጠቀም ሳይችል ሲቀር ነው።
አንድ ሰው የስኳር ህመም አለው የምንለው በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ከሚገባው በላይ ከፍ ብሎ ሲገኝ ነው።
በደም ውስጥ የሚገኘው የስኳር መጠን ከመጠን በላይ ከፍ ብሎ የሚገኘው ደግሞ ቆሽት የተባለው የሰውነት ክፍል ኢንሱሊን የተሰኘው ንጥረ-ቅመም በእንግሊዝኛ አጠራሩ ሆርሞን በበቂ ሁኔታ ወይም ደግሞ ጭራሹኑ ማመንጨት ሲያቅተው ነው።
ዋና ዋናዎቹ የስኳር ህመም አይነቶች ሶስት ሲሆኑ አንደኛው አይነት የስኳር ህመም ኢንሱሊን የሚባለው ሆርሞን አለመመረት፣ ሁለተኛው አይነት የስኳር ህመም የተመረተውን ኢንሱሊን ሰውነታችን መጠቀም ሳይችል ሲቀር ሶስተኛው አይነት ደግም በእርግዝና ጊዜ የሚመጣ የስኳር ህመም ናቸው።
በአዲስ ህይወት ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዶ/ር ኤደን ተ/ማርያም የስኳር ህመምን ምልክቶች አስረድተውናል።
በቤተሰብ ውስጥ የስኳር ህመም መኖር ፣ ዘረመል ፣ የእድሜ መጨመር በስኳር የመያዝ እድላችን የሚጨምሩ ቢሆንም አንዳንድ የአኗኗር ሁኔታዎች ለሁለተኛው አይነት የስኳር ህመም ተጋላጭነትን ይጨምራሉ።
የህክምና ባለሙያዋ እንደሀገር ስኳርን የመመርመሪያ ኪቶች እጥረት እንዳለ ጠቁመው የመድሃኒት አቅርቦት ላይ መንግስት መስራት ይኖርበታል ብለዋል።
5.4 ገደማው የህብረተሰብ ክፍል ለስኳር በሽታ ተጋላጭ መሆኑን ዶ/ር አትኩሬ ደፋር በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የስርዓተ ጤና ከፍተኛ ተመራማሪ ነግረውናል።
ከዓለም የጤና ድርጅት የጥናት ስታንዳርድ በተቃራኒ በእኛ ሀገር ስኳርን የተመለከተ ጥናት ሲካሄድ ከ 18 ዓመት በታች ያሉትን ህጻናት ያካትታል በለውናል።
እንደ ምክንያት ያስቀመጡትም በሀገራችን ያሉ ህጻናት በስኳር ህመም እየተዳረጉ መሆኑን ነው።
ከዓለም ሕዝብ 422 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ይህ ህመም እንዳለባቸው ይገመታል።
ይህ አሃዝ ከዛሬ 40 ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር በአራት እጥፍ ከፍ ያለ ነው ይላል የዓለም ጤና ድርጅት።
በሀገራችን ስንመለከት ደግሞ 3 ነጥብ 2 በመቶ ኢትዮጵያዊያን የስኳር ህመምተኞች ናቸው።
የስኳር ህመም የሚያስከትላቸው ችግሮችም የአንጎል ምት (stroke )፣ አይነ ስውርነት፣ የልብ መድከም፣ የኩላሊት መድከም ፣ የእግር መቆረጥ እና የቁስል ቶሎ አለመዳን ይጠቀሳሉ።
ጤነማ አመጋገብ መከተል፣ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ከልክ ያለፈ ውፍረት ማስወገድ፣ የሚጠራጠሩ ከሆነ የስኳር መጠንን መለካት እና የህክምና ምክሮችን መከታተል ከበሽታው መከላከል ያስችላል።
በመቅደስ እንዳለ
2022-06-10
