ጥንታዊ የአለም ታሪክን መልክ መቀየር የቻለ ጦረኛ ነው። ከአለም እውቅ እና ዝነኛ የጦር ጀነራሎች አንዱ ነው። ከፈላስፋው አርስቶትል ትምህርትን ከንጉስ አባቱ የጦር ክህሎትን ተምሯል። ከግሪክ መቄዶንያ ተነስቶም እስከ ግብጽ ብሎም ምስራቅ ኤስያ ህንድ ድረስ ግዛቱን ማስፋት ችሏል። ለ13 አመታት ንጉስ የነበረው ይህ ሰው ታላቁ አሌክሳንደር ነው። ሰፊ ግዛትን በጦር አሸናፊነት የጠቀለለው አሌክሳንደር ሞቱ በ33 አመቱ በዛሬው እለት በ323 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ እንደሆነ መዛግብት ይናገራሉ።
የመቄዶንያ ንጉስ የነበረው አሌክሳንደር ሶስተኛ ታላቁ አሌክሳንደር ተብሎ ይታወቃል። መነሻው በጥንታዊዋ መቄዶን የሆነው አሌክሳንደር በ13 አመታት ውስጥ የአለም ጥንታዊ ታሪክን በሃይል መቀየር ችሏል።
አሌክሳንደር ውልደቱ በ356 ቅ.ል.ክ. ከመቄዶንያ ንጉስ ፊሊፕ ሁለተኛ እና ኦሎምፒያስ በፔላ በጥንታዊዋ መቄዶንያ ዋና ከተማ ነው። አሌክሳንደር ከቀደምት ፈላሳፎች አንዱ ከሆነው አሪስቶትል የዘመኑን ትምህርት ተከታትሏል።በ336 ቅ.ል.ክ. ከአባቱ መገደል በኋላ ተቀናቃኞቹን በፍጥነት በማጥፋት አሌክሳንደር የመቄዶንያ ንጉስ ሆኗል።
የዘመኑን ትምህርት ከፈላስፋው አርስቶትል ወታደራዊ ክህሎትን ከንጉስ አባቱ የተማረው አሌክሳንደር በ16 አመቱ ጦር መምራት ጀምሯል። ከሁለት አመት በኋላ ደግሞ በቸሮኒያ ጦርነት የአባቱን ትልቅ የጦር ሰራዊት በመምራት ግሪክን አሸንፎ በመቄዶንያ አስተዳደር ስር እንድትሆን አድርጓታል።
ከአባቱ ሞት በኋላ የመቄዶንያ ዙፋን ላይ መቀመጥ የቻለው አሌክሳንደር በግሪክ የመቄዶንያን አስተዳደር ካጸና በኋላ በዘመኑ ግዙፍ የነበረውን የፐርሽያ ግዛትን ለመቆጣጠር ተንቀሳቀሰ። የጦር ሰራዊቱን እየመራ ወደ ፐርሽያ ግዛቶች የተጓዘው አሌክሳንደር የፐርሽያ ግዛቶችን ያለ አንድ ሽንፈት በእጁ ማስገባት ቻለ። ትልቁ የጦርነት ድሉንም በጓጋሜላ ጦርነት እንዳስመዘገበ ይነገራል።
በኤሽያ ማይነር( ቱርክ) የሚገኙ ግዛቶች፣ ሶሪያ ብሎም ግብጽ በአሌክሳንደር እጅ ወደቁ። የ25 አመቱ አሌክሳንደር የመቄዶንያ ንጉስ፣ የግሪኮች መሪ፣ የኤሽያ ማይነር ጌታ፣ የግብጽ ፈርኦን በመሆን ታላቅ ንጉስ ሆነ።
ከፐርሽያ ዘምቻው በኋላ ወደምስራቁ ክፍል ተንቀሳቀሰ። አፍጋኒስታንን፣ መካከለኛው ኤስያን ብሎም ሰሜን ህንድን ጠቀለለ።
አሌክሳንደር እንደንጉስ፣ እንደጦር አዛዥ፣ ፖለቲከኛ፣ ምሁር ብሎም አሳሽ በመሆን የጦር ሰራዊቱን በመምራት 70 የሚደርሱ ከተሞችን በመያዝ ወደ ሶስት አህጉራት የተዘረጋ ግዛት መስርቷል።
ከአውሮፓ ግሪክ እስከ አፍሪካ ግብጽ ብሎም ኤስያ ህንድ ድረስ በአሌክሳንደር ግዛት ስር ተጠቃለዋል። በሰፊ አለም አቀፍ የንግድ ሰንሰለትም እንዲተሳሰሩ በር ከፍቷል። በአሌክሳንደር የገናናነት ዘመንም ሆነ በኋላ የግሪክ ቋንቋ እና ባህል እንዲስፋፋም ሆኗል። የግዛቶቹን ታሪክ መቀየር የቻለው አሌክሳንደር የባህል መለዋወጥ እንዲኖርም በር ከፍቷል።
ከስምንት አመታት ረዥም የጦርነት ጉዞ በኋላ ሰራዊቱ ደክሞ ወደፊት ለመጓዝ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። አስቸጋሪ በሆነው የማካራን በረሃም ሰራዊቱን መራቸው።
ታላቁ አሌክሳንደር በጦር አዋቂነት በምሳሌነት የሚጠቀስ በታሪክ ገናና ከሆኑ ሰዎች አንዱ ነው። ለ13 አመታት ከሰራዊቱ ጋር በመሆን በጦርነት አሳልፏል። በነዚህ አመታት ውስጥ ሰራዊቱ እርሱን ከመከተል እምቢ ያለው አንድ ጊዜ ብቻ መሆኑም የገነባውን ታማኝነት ያሳያል።
ሰራዊቱን ወደ ኋላ መልሶ የነበረው አሌክሳንደር ባቢሎን(ባሁኑ ኢራቅ) ከደረሰ በኋላ ሰራዊቱ ጋር ወደ ግብጽ የሚመለስበትን መርከብ ማሰራት ጀመረ። ግና የመርከብ ስራው ወደ መደምደሚያው ሲቃረብ በ323 ቅ.ል.ክ. በ33 አመቱ ታሞ ሞተ።
ተተኪውን ያልመረጠው አሌክሳንደር ከሞተ ከአመት በኋላ ሰራዊቱ እና ግዛቱ ብዙ ተዋጊ ቡድኖችን ፈጠረዋል።
የተዋጋለት ግዛትም ተከፋፋሏል።
አሌክሳንደር ግን በጥንቱ የአለም ታሪክ ከተከሰቱ ገናና መሪዎች አንዱ ተደርጎ ይታሰባል።
በአብርሃም በለጠ
2022-06-13
