የትራንስፖርት ቢሮ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ላይ የታሪፍ መጠን አሻሽላለሁ አለ። የዓለም አቀፍ ነዳጅ ምርቶች መሸጫ ዋጋ እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በታህሳስ ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ አዲስ የዋጋ ማስተካከያ መደረጉ ይታወሳል። ቤንዚን ላይ በተደረገው የዋጋ ማስተካከያ ባለፈው ወር ሲሸጥበት ከነበረው ዋጋ ጭማሪ በማድረግ በሊትር 31 ብር ከ74 ሳንቲም እንዲሸጥ ተወስኗል። ይህንንም ተከትሎ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ በህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የታሪፍ ማሻሻያ ለማድረግ ጥናቱን እያጠናቀቀ ነው፡፡ በቀጣይ ቀናትም የታሪፍ መጠኑን ይፋ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ከ አዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡ በመሆኑም የታሪፍ ማሻሻያው ተጠናቆ ይፋ እስኪሆን ቀደም ሲል በነበረው የታሪፍ ዋጋ አገልግሎቱ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ በከተማዋ በህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ አሽከርካሪዎችም የታሪፍ መጠኑ ይፋ ሳይሆን ምንም ዓይነት ዋጋ ባለመጨመር አገልግሎቱን እንዲሰጡ ቢሮው አሳስቧል፡፡
በሀገሬ ቲቪ
2021-12-10
