አማራ ባንክ አክሲዮን ማህበር ወደ ስራ ለመግባት ዝግጅቴን ማጠናቀቄን እወቁልኝ ብሏል።
ባንኩ ዛሬ በሰጠው መግለጫ የፊታችን ቅዳሜ ሰኔ 11 የባንኩን ዋና መስሪያ ቤት ጨምሮ አገልግሎት ለመስጠት የተዘጋጁ ቅርንጫፎቼን አስመርቃለው ብሏል።
ባንኩን ወደ ስራ ለማስገባት በተደረጉ በርካታ ተግባራቶች ላይ መግለጫ የሰጡት የባንኩ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መላኩ ፈንታ ብሄራዊ ባንክ መፈረም ይችላሉ ያላቸውን ከ146 ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖች የማስፈረም ስራውን ረዘም ባሉ ግዜያት መከወኑን አንስተው መፈረም ከሚችሉት ውስጥም በአግባቡ ፊርማ ያላኖሩ ባለ አክሲዮኖች መኖራቸውን አስረድተዋል።
“ወደ 44 ሺህ የሚሆኑ አክሲዮን የገዙ ግለሰቦች በተለያየ ምክንያት ይቀራሉ። እነዚህን በሚቀጥሉ ግዜያት ቦርዱ በሚወስነው እና ጥቅላላ ግጉባኤው በሚወስነው መሰረት የሚስተናገዱ ይሆናል።”
እነዚህን ባለአክሲዮኖች የባንኩ ቦርድ እና ጠቅላላ ጉባኤው በሚወስነው መሰረት ወደ ባንኩ ባለቤትነት የማስገባቱ ስራ ይቀጥላል ብለዋል።
ባንኩ ማሟላት ያለበትን ተግባራቶች በማሟላት ባንኩን በኃላፊነት የሚመሩ የስራ ኃላፊዎችን ለብሄራዊ ባንክ አቅርቦ በማፀደቅ ወደ ትግበራ መግባቱም በመግለጫው ላይ ተካቷል።
ቅዳሜ በይፋ ስራ የሚጀምረው ባንኩ ከዛሬ የሚጀምር፤ የደም ልገሳን እና የኪነጥበብ ምሽትን ጨምሮ የባንኩን ስራ መጀመር የሚያበስሩ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀቱን ከመድረኩ ሰምተናል።
ባንኩ ዋና መስሪያ ቤቱን በሚያስመርቅበት እለትም የተለያዩ ስጦታዎች መዘጋጀታቸውን የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሄኖክ ከበደ ተናግረዋል።
“የፊታችን ቅዳሜ ዋና መስሪያ ቤታችንን ስናስመርቅ በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ለሚገኙ የአንበሳ ባስ ተጠቃሚዎች ነፃ ትራንስፖርት ተዘጋጅቷል። እንዲሁም በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች ባሉ ሆስፒታሎች ለሚወልዱ እናቶችም ስጦታዎች ተዘጋጅተዋል።”
በመላው ሀገሪቱ 70 ያህል ቅርንጫፎችን በመክፈቻው እለት ወደ ስራ የሚያስገባው ባንኩ፤ ከእነዚህም ውስት በርከት ያሉት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ እንደሆኑ ተጠቁሟል።
ባንኩ በሀገሪቱ የሚገኙ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማገዝ መዘጋጀቱን ያነሱት የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢው አቶ መላኩ ፈንታ ናቸው።
“ባንካችን አነስተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ቆጥበው የሚጠቀሙበት እና ሃሳቦችን ወደ ስራ ለመለወት እንዲችሉ የሚያስችል ዳይሬክቶሬት የተቋቋመበት ነው።”
አማራ ባንክ የፊታችን ሰኔ 11 የዋና መስሪኦያቤቱን እና ቅርንጫፎቹን በማስመረቅ ወደ ስራ ይገባል።
በሳምሶን ገድሉ
2022-06-13
