ሀገሬ ቲቪ

የባሕር ሲሳይ እየኾኑ ያሉት ፈላሲያን

ባላቸው ምጣኔሀብታዊ አቅም ጎልበተዋል፤ ከራሳቸው ዜጎች ባለፈ ለሌሎች ሀገራት ዜጎች የእንጀራ ገመድ ኾነዋል ወደ ሚባልላቸው የአውሮፓ ሀገራት የሚተሙ ፈላሲያን ቁጥር እንደኛ አቆጣጠር 2008 ከነበረው ቁጥር የቀነሰ ቢሆንም የሟቆች ቁጥር ግን ከምንጊዜውም በላይ እንደጨመረ የተባበሩት መንግሥታት የፍልሰተኞች ኤጀንሲ ባሰባሰው መረጃ አስታውቋል።

እንደኛ አቆጣጠር በ2008 የሜዲትራኒያን ባሕርን የሚያቋርጡ ፈላሲያን ቁጥር ከ 1ሚሊዮን በላይ ተሻግሮ ነበር። ይኽ ቁጥር ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት ቀንሶ ነበር። ባለፈው ዓመት ብቻ የሜዲትራኒያንን ባሕር በሟቋረጥ አውሮፓ ለመግባት የሞከሩ ፈላሲያን ቁጥር ከ 1 መቶ23 ሺህ በላይ ኾኖ ተመዝግቧል። ይኽ ቁጥር ከሌሎች ተመሳሳይ ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው።

የፈላሲያኑ ቁጥር የቀነሰ ይምሰል እንጂ የሟቆች ቁጥር በእጅጉ በዝቷል። ባለፈው ዓመት ብቻ ከ 3231 ፈላሲያን የሜዲትራኒያን እና የሰሜን መዕራብ አትላንቲክ ባሕር ሲሳይ ኾነዋል። በእኛ አቆጣጠር በ2010 እስከ 2012 ባሉት ሦስት ዓመታት ከ 5ሺህ 6 መቶ በላይ የሟቆች ቁጥር ተመዝግቧል።

ምንአልባትም በሳህራ በርሃ እና በተለያዩ ድንበሮች የሞቱ በርካታ ፈላሲያን እንደሞኖሩ ነው የተነገረው። የተባበሩት መንግሥታት የፍልሰተኞች ኤጀንሲ እነዚኽን በሕይወት ላይ ቁማር በማሲያዝ የሚደረጉ አደገኛ ጉዞዎች የተመለከተ ማስጠንቀቂያ ስሰጥ ቆይቻለሁ ብሏል።

ይኹን እንጂ ፈላሲያኑ ተቋማት ከሚሰጡት ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ በላይ በየሀገራቸው ያለው ግጭት፣ አመጽ እና የሀገራቸውን ሀብት የመቋደስ ዕድል ተነፍጎአቸው የበይ ተመልካች የመኾናቸው እውነታ እንደሚጎላባቸው በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

አብዛኞቹ ፈላሲያን ከአፍሪካ የሚነሱ ሲኾን በተለይም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያሉ ሀገራት ማለትም ኢትዮጵያን ጨምሮ ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን ጅቡቲ እንዲሁም መተላለፊያ የኾነችው ሊቢያ በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው። ከነዚኽ ሀገራት በየጊዜው ሕጋዊ ባልኾነ መንገድ የሚነሱ ፈላሲያን በሜዲትራኒያን ባሕር ውስጥ ብቻ ሳይኾን እየሞቱ ያሉት ረጅም መንገድ በእግር በሚያቋርጡት በርሃ ላይም ነው።

በእነዚኽ ያለቀባሪ በሚቀሩ ዜጎች ታዲያ የፈላሲያን ሞት ቁጥር በእጅጉ ሊጨምር እንደቻለ በጉዳዩ ላይ የወጣው ሪፖርት ይገልጻል። ሕይወትን ከማጣት ባለፈ ሕገወጥ ደላሎች እና ፍልሰተኛ አዘዋዋሪዎች የሚደርስባቸው ስቃይ እና ድብደባ በእጅጉ የከፋ እንደኾነ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል አኹንም በዚኽ ሪፖርት ተካቷል።

የተባበሩት መንግሥታትም ጉዳዩ ከዕለት ወደ ዕለት አሳሳቢ እየኾነ በመምጣቱ የፈላሲያኑን ሕይወት የሚታደግ እርምጃ እንዲወሰድ ስወተውት ቆይቻለሁ ብሏል።

2ነጥብ 5 ሚሊዮን ስኩዬር ኪሎሜትር የሚሰፋውን እና 1500 ሜትር ጥልቀት ባለው በዚህ አደገኛ ባሕር ላይ መናኛ ጀልባን በመጠቀም የሚጓዙ ፍልሰተኞች ቁጥር ቀላል አይደለም። በዓመት ከ 3ሺህ በላይ ሰዎች በመስጠም አደጋ ይሞታሉ አሊያም ደብዛቸው ይጠፋል።

በሙሉጌታ በላይ
2022-06-13