ሀገሬ ቲቪ

‹‹በሚተካ ደም ሕይወትን እናድን ››

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት 1 ደም ለጋሽ የሦስት ሰዎችን ሕይወት ማትረፍ ይችላል ታዲያ ዓለማችን በየቀኑ 38 ሺሕ የደም ለጋሾችን ትፈልጋለች ምን ያህሎቻችን ደም ለመስጠት በጣቢያዎች እንገኝ ይሆን ይሄ ለሁላችንም ጥያቄ ነው፡፡

ለጋሾች ለማበረታታት እና ምስጋና ለመቸር እንዲሁም ደም ለጋሾችን ቁጥር ለመጨመር በሚል በየዓመቱ ሰኔ 7 የደም ለጋሾች ቀን ይከበራል፡፡ዘንድሮ ‹‹ደም መለገስ የአብሮነት መገለጫ ነው፤ ተባብረን ህይወት እናድን›› በሚል መሪ ቃል በመላው ዓለም ተከብሮ ውሏል፡፡

የዓለም የደም ለጋሾች ቀን ዓለም አቀፋዊ ጭብጡ ደማቸውን ለማያውቋቸው ሰዎች የሚለግሱ ከራስ ወዳድነት ነፃ ለሆኑ ግለሰቦች እውቅና መስጠት ነው ፡፡

ሀገሬ ቴቪ ያናገራቸው የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ባለሙያ አቶ ንጋቱ አላመንታ የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው መስፈት መሰረት አንድ ሀገር የዜጎቿን 1 በመቶ ያህል ደም መሰብሰብ አለበት ይላል ይሁን እንጂ በዚህ ዓመት እንኳን ብንመለከት 313ሺሕ 762 ዩኒት ደም ብቻ ነው የተሰበሰበው፡፡ደማችንን ባንለግሰውም ከሰውነታችን መወገዱ ስለማይቀር ለሰው ህይወት እንሁን ይላሉ ባለሞያው፡፡

አንዳንዱ ቦታዎችን ባለማወቅ አንዳንዱ ደግሞ ደም መለገስ በመፍራት ጭምር ይሸሻል፤ይሁን እንጂ መረጃው በትክክል ከደረሰን ለመለገስ ፍቃደኞች ነን የሚሉም አልጠፉም፡፡

ደም ለመለገስ ፍቃደኛ የሆናችሁ አዲስ አበባ ላይ 12 የደም መለገሻ ቦታዎች እንዲሁም በክልሎች ደግሞ የደም ባንኮች በመሄድ ለግሱ ብለዋል፡፡

ደም በማጣት ህይወታቸው የሚያጡ ዜጎችን በማሰብ የማንጠቀምበትን ደም እንለግስ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ 118.5 ሚሊዮን ዩኒት የተለገሰ ደም ይሰበሰባል፡፡

በፍሬህይወት ታደሰ
2022-06-14