ዛሬ ላይ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ በብዙ መሻሻል ውስጥ አልፎ አለምን ከጫፍ እስከ ጫፍ አዳርሷል። በዛሬዋ እለት በ1943 ነበር የአሜሪካ የህዝብ ቆጠራ ቢሮ የመጀመሪያውን ለንግድ የተመረተ ዩኒቫክ የተሰኘ ዲጂታል ኮምፒውተርን ያስተዋወቀው። የመጀመሪያውን ኤለክትሮኒክ ዲጂታል ኮምፒውተርን በሰሩ የኢንጂነሮች ቡድን የተገነባው ይሄው ግዙፍ ኮምፒውተር ላሁኖቹ ኮምፒውተሮች ከግንባር ቀደሞቹ አንዱ ነው። የዛሬው እለቱን ከታሪክ ትኩረቱን ከዚሁ ላይ ያደርጋል።
ዛሬ ላይ በብዙ መልኩ ተሻሽሎ ከእጃችን የደረሰው የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ የጅማሮ መንደርደሩ ከጥንት የጀመረ እንደሆነ ይነገርለታል። ጥንት አባከስን ባቢሎናውያን፣ቻይናውያንና ሮማውያን ለማስሊያነት ሲጠቀሙ ዲጂትን መጠቀማቸው የኮምፒውተር መነሻ ነው ይባልለታል።
የኮምፒውተር ግኝት የአለምን ቀጣይ ርምጃ ቀይሮታል።
መካኒካዊ የሆነ የማስሊያ ኮምፒውተር በፈረንሳይ በ1930ዎቹ መሰራት ችሏል።
በሁለተኛው የአለም ጦርነት በዩናይትድ ስቴትስ መንግስት በጀት ኢንያክ ( ENIAC) የተሰኘ ኤለክትሮኒክ ዲጂታል ኮምፒውተር እንዲሰራ ሆኗል። ይሄው ኮምፒውተር ጠቅላላ የኮምፒውተር አገልግሎት እንዲሰጥ የተሰራ የመጀምሪያው ግዙፍ ኮምፒውተር ነው። ይሄው ኮምፒውተር የተሰራው በጄ. ፕሬስፐር ኤከርት እና ጆን ማቹሊ የኢንጂነሮች ቡድን ነው። የኢንጂነሮቹ ቡድን ኮምፒውተሩን መገንባት የቻሉት በፔንሲልቫኒያ ዩኒቨርሲቲ ነው።
ይሄው በአሜሪካ የተገነባው ኮምፒውተር በሙሉ መጠሪያው ‘Electronic Numerical Integrator and Calculator’ የሚል ስያሜ የነበረው ሲሆን የ500 ሺህ ዶላር ወጭ ወጥቶበታል። ከ4 ሺህ ሜትር በላይ ርዝመት የነበረው ሲሆን 17 ሺህ ቫኪውም ቲውብ እና 6 ሺህ ያክል ማብሪያና ማጥፊያዎችን የሚጠቀም ነበር።
ይሄው ኢንያክ( ENIAC) የተሰኘ ኮምፒውተር በሎስ አላሞስ ቤተ ሙከራ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማስላት ያገለገለ ሲሆን በ1938 በይፋ ተዋውቋል።
የዚህ ግዙፍ ኮምፒውተር ስኬታማነትን ተከትሎ ኤከርት እና ማቹሊ ወደ ግል ቢዝነስ ለመግባት ወሰኑ። ኤከርት-ማቹሊ ኮምፒውተር ኮርፖሬሽንን መሰረቱ። ኢንጂነሮቹ አቅም ያነሳቸው የንግድ ሰዎች በመሆናቸው የታገሉለትን ድርጂታቸውን ሬሚንግተን ራንድ የቢሮ እቃዎች ድርጅት ገዛው።
በዛሬዋ እለት ከ71 አመታት በፊት በ1943 ሬሚንግተን ራንድ የመጀመሪያው ኮምፒውተሩን ዩኒቫክ1(UNIVAC1)ን ለአሜሪካ የዩናይትድ ህዝብ ቆጠራ ቢሮ አቀረበ። ዩኒቨርሳል ኮምፒውተር ተብሎ የሚጠራው ይሄው ግዙፍ ኮምፒውተር ከ7 ሺህ ኪ.ግ. በላይ ክብደት የነበረው ነው። 5 ሺህ ቫኪውም ቲውቦችን የሚጠቀመው ይሄው ኮምፒውተር በሰከንድ አንድ ሺህ የሚደርሱ ካልኩሌሽኖችን መስራት የሚችል ነበር።
ይሄው የተሻሻለው ኮምፒውተር በጊዜው በዩናይትድ ስቴትስ ሴንሰስ ቢሮ ለንግድ የቀረበ የዲጂታል ኮምፒውተር ነው።
የመጀመሪያዎቹ ግዙፍ የሆኑ እና ቫኪውም ቲውብን የሚጠቀሙት ኮምፒውተሮች በ1940ዎቹ እና 50ዎቹ በትራንዚስተር ኮምፒውተሮች ተተክተዋል።
ትራንዚስተር የሚጠቀሙ ኮምፒውተሮች ቫኪውም ቲውብ ከሚጠቀሙት ኮምፒውተሮች ይልቅ በመጠናቸው ትንሽ፣ ብዙ ሃይል የማይፈጁ ብሎም በሺህ የሚቆጠሩ ስራዎችን በሰከንድ ማስላት መቻላቸው ተመራጭ አድርጓቸዋል። የመጀመሪያዎቹ የነዩኒቫክ አይነት ኮምፒውተሮችም በሂደት ከገበያው ወጥተዋል።
ከማይክሮ ፕሮሰሰር መምጣት ወዲህ ደግሞ በእጅ መያዝ እስከሚችሉ ፈጣን ኮምፒውተሮች ደርሰናል።
የዚህ ሁሉ የኮምፒውተር መሻሻል መነሻ ግን እነዚያ የመጀመሪያዎቹ ግዙፎቹ ኮምፒውተሮች ናቸው።
በአብርሃም በለጠ
2022-06-14
