ሀገሬ ቲቪ

ልጁን ለፍርድ ያቆመው አባት

ግዜ እዚህ አደረሰን እንዴ ባዮች በርክተዋል። ምክንያታቸው ደግሞ በቻይና ሆነ ተብሎ በማህበራዊ ገፀ ድሮች ላይ የቡና መጠጫ የሆነው ነገር ነው። ሰውየው ባለቤቱን ከፈታ በኋላ በባለቤቱ እና ከሱ ባልተወለደው ባሳደገው የባለቤቱ ልጅ ላይ የክስ ፋይል ይከፍታል።

የክሱ ፋይል ምን ቢሆን መልካም ነው?

ከቀድሞ ባለቤቴ ጋር አብረን በኖርንባቸው ዓመታት ለልጇ ማሳደግያ ያወጣሁት ገንዘቤ ይመለስልኝ። የሚል። ሰውየው ታንግ ይባላል የቾንግኪንግ ሰው ነው።

ያኔ በ2001 ዓ.ም የቀድሞ ባለቤቱን ሲያገባት የ10 ዓመቱን ሊዩንም እንደ ልጁ አምኖ ሊቀበል እና ሊያሳድገው ቃል ገብቶም ነበር። ታዲያ የባለትዳሮቹ እህል ውሃ ከ12 እንቁጣጣሽ ሊዘል አልቻለም በ2013 ዓ.ም ትዳር በቃን ሲሉ ለመለያየት ወስነው ይፋታሉ።

ሚስቱን የፈታው ታንግ ፈት ከሆነበት ሰዐት ጀምሮ አንድ ነገር እረፍት ይነሳዋል። ያሳደገው ልጁን እዚህ እንዲደርስ ለልጁ ያወጣው ገንዘብ ያንገበግበው ይገባል። ግዜም አላጠፋ ወዲያውኑ ወደ ፍርድ ቤት ያቀናል።

የቀድሞ ባለቤቱ እና ያሳደገው ልጁ 35,200 የቻይና ገንዘብ ወይንም ዩዋን ለልጁ ማሳደጊያ አውጥቼዋለው ይመልሱልኝ ሲል። የፍርድ ቤቱ ሂደት ቻይና በሀገሯ በምትጠቀመው ቲውተር መሰል ማህበራዊ መገናኛ ላይ ከተለጠፈ በኋላ በርካቶችን አነጋግሯል። “ልጁን ለ10 ዓመታት ካሳደገ በኋላ እንኳን, እንደ ልጅ አድርጎ የተቀበለው አይመስልም። ይህ በጣም ያሳዝናል” ሲል አንድ ሰው አስተያየቱን በዚሁ መድረክ ሰጥቷል።

ባለፈው ወር ጉዳዩን ለማየት የተሰየመው በቾንግኪንግ አካባቢ ፍርድ ቤት ታንግ ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አድርጎታል። ፍርድ ቤቱ ታንግ ካሳ ይከፈለኝ ያለው በፈቃዱ ላወጣቸው ወጪዎች ነውና ጥያቄው አግባብነት ያለው አይደለም ሲል።

የፍርድ ቤቱ ዳኛም እንዲህ አሉ ታንግ ሊዩን ለመደገፍ እና እንደልጅ ለማሳደግ መርጧል። ያለ ማንም አስገዳጅነት 18 ዓመት ካለፈው በኋላም ቢሆን ታንግ ሊዩን መደገፉን አላቆመምም ነበር ሲሉ። የዩንቨርሲቲ ትምህርት ክፍያውንም ቢሆን ክፈልለት ያለው የለም ግን ታንግ በፈቃዱ አድርጎታል ሲሉም አክለዋል።

ቻይና በህጓ ላይ ወላጆች ልጆቻቸው 18 ዓመት ከሞላቸው በኋላ ወጪያቸውን እንዲሸፍኑ አያስገድድም። 18 ዓመት የሞላው ልጅ ሙሉ ሰው ነው እና ጥሮ ግሮ እራሱን ማኖር ይችላል ይላል የቻይናው ህግ። አይ ዘመን ማለት ይሄንን አይደል።

በሳምሶን ገድሉ
2022-06-14