ሂዩማን ራይትስ ዋች የህወሓት ኃይሎች በአማራ ክልል ንጹሃንን በጅምላ መግደላቸውን ገለጸ፡፡ በክልሉ ጭና እና ቆቦ አካባቢዎች ባለፈው ዓመት ከነሐሴ 25 እስከ ጳጉሜ 4 በነበሩት አስር ቀናት ውስጥ ነው ግድያው የተፈጸመው፡፡ እንደ ሂዩማን ራይትስ ዋች ሪፖርት ከሆነ በመጀመሪያ የህወሓት ኃይሎች ጭና ወደተባለችው መንደር በመግባት በአምስት ቀናት ውስጥ በ15 የተለያዩ ሥፍራዎች 26 ሰላማዊ ሰዎችን መግደላቸውን ከነዋሪዎች መረጃ አግኝቷል፡፡ በተመሳሳይም በቆቦ ከተማ በአራት የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የትግራይ ኃይሎች 23 ሰዎችን እንደገደሉ የዓይን እማኞች ለሂዩማን ራይትስ ዋች ገልጸዋል፡፡ የሂማን ራይትስ ዋች የቀውስና የግጭት ጉዳዮች ዳይሬክተር ላማ ፋኪህ የትግራይ ኃይሎች ስለተፈጸሙት የግፍ ግድያዎች አስከፊነትና ስለህወሓት ቸልተኝነት ተናግረዋል፡፡ በትግራይ እና በአማራ ክልሎች ተፈጽመዋል ስለተባሉ የጦር ወንጀሎች በገለልተኛ አካል ማጣራት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በመስከረም እና በጥቅምት ወር በጭና ተክለሐይማኖት መንደርና ቆቦ ከተማ የጠየቃቸው 19 እማኞች ጭና እና ቆቦ ውስጥ የትግራይ ኃይሎች በአጠቃላይ 49 ሰላማዊ ሰዎችን ሲገድሉ ማየታቸውንና ከሟቾቹም የ44ቱን ሰዎች ሥም ጠቅሰዋል ፡፡ የሟቾች ቁጥር ከዚህ ሊልቅ እንደሚችልም ሂዩማን ራይትስ ዎች በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
በሀገሬ ቲቪ
2021-12-10
