በዓለም ምጣኔ ሀብት ላይ ከፍተኛ ቦታ ያላት ሀገር ናት። በደረጃ ከተቀመጠችም በምጣኔሀብቷ የኹለተኛ ደረጃን ትይዛለች። ቻይና። ከጊዜ ወደ ጊዜ ይኽው እድገቷ የዓለም ቀልብ የያዘ ሀገራት እጃቸውን በአፋቸው እንዲጭኑ ያደረገ ነበር። ነገር ግን ከኮቪድ 19 ቫይረስ መከሰት በኋላ ይኸው ዕድገቷ እንደልቡ ሊራመድላት አልቻለም። የቫይረሱ ምንጭ ደግሞ ራሷ መኾኗ በብዙ መልኩ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ከቷታል። በዚኽ የተደናገጠችው ቻይና ምርቱም ኾነ ዕድገቱም አሳሳቢ አይደለም በማለት ጠንከር ያለና እስከዛሬ የዘለቀ የዕንቅስቃሴ ገድብ እና የምርት ማቆምን አድርጋለች።
ይኽ እርምጃዋ ታዲያ ከራሷ አልፎ የዓለም ምጣኔሀብት ላይ የራሱን የኾነ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ አልቀረም። የዓለም ባንክም በአኹን ወቅት ግሎባል ኢኮኖሚው አሊያም የዓለም ምጣኔ ሀብት በእጅጉ እየተፈተነ ነው ብሏል። ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ባለፈ የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት መከሰት ችግሩ እንደብረት የጠነከር እንዲኾን አድርጎታል። ይኽ በእንዲኽ እያለ በቻይና የተጣለው ጠንከር ያለ የእንቅስቃሴ ገደብ ምርት በስፋት እንዳይመረት ሳንካ በመኾኑ የዓለም ባንክ ለቻይና እባክሽ ምርት ወደ ማምረት ግቢና የተከሰተውን ችግር አቅልዪ የሚል ተማጽዕኖ መሰል ጥያቄ እያቀረበ ይገኛል።
አኹን ላይ ታዲያ የበርካቶችን ጆሮ የያዘ መረጃ ከወደቻይና እየወጣ ይገኛል። ሀገሪቱ የእንቅስቃሴ ገደቦችን በማላላት ለበርካታ ጊዜአት ከምርት ጋር ተነፋፍቀው የቆዩ ኢንዱስትሪዎቿን ዳግም ወደ ሥራ እንዲገቡ እያደረገች ነው ተብሏል።
የኢንዱስትሪ ምርት በሚያዝያ ወር 2ነጥብ9 በመቶ ካሽቆለቆለ በኋላ ባለፈው የግንቦት ወር የኢንዱስትሪ ምርት 0ነጥብ7 በመቶ ማንሰራራት አሳይቷል ሲል የሀገሪቱ ብሔራዊ ስታስቲክስ ቢሮ አስታውቋል።
ይኽው በኢንዱስትሪው ዘርፍ የታየው መነቃቃት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ያደረገው የእንቅስቃሴ ገድብ በማላላት እና በጠንካራ የዓለም አቀፍ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ነበር።
ባለፈው ግንቦት ወር የቻይና የወጪ ምርት በሁለት ዲጂት አድጓል። የኢንዱስትሪዎች እንደገና ወደ ምርት መግባት እና ምርትን በማጓጓዙ ያሉ ተግዳሮቶች ቀለል ማለታቸው ሊመጣ የሚችለውን ስጋት አስወግዶታል።
ከዓመት በፊት ለማገገም ሲጥር የነበረው የሀገሪቱ የመአድን ዘርፍ ባለፈው ግንቦት ወር 7 በመቶ አድጓል። በዚኽም ዘርፉ ከለሎች በተለየ ግንባር ቀደም መኾን ችሏል።
የሀገሪቱ ሹማምንት በአጠቃላይ፣ የሀገሪቱ ምጣኔሀብት ዕድገት ኮቪድ19 ወርውርሽኝ ያስከትለውን አሉታዊ ተፅእኖ በማሸነፍ ከግንቦት ወር ጀምሮ በፍጥነት እያገገመ ነው ማለታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል። አኹንም ቢኾን ለምጣኔ ሀብቱ እድገት የሚረዳ ፖሊሲ በመቅረጽ ምጣኔሀብታችንን እናጎለብታለን ብለዋል የሀገሪቱ ሸማምንቶች።
ይኽ ችግር አህጉራችንን ጠበብ ሲልም ቀጠናችን ላይ የራሱን ተጽ ዕኖ አሳድሯል።
ባለፉት 15 ዓመታት ቻይና ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ዋነኛ የኢኮኖሚ አጋር ሆናለች። ቻይና የአፍሪካ አህጉር ትልቁ የንግድ አጋር እና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምንጭ ነች።
ኮቪድ-19 ቻይና ከአፍሪካ ጋር ባላት ግንኙነት ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ በዋናነት ኢኮኖሚያዊ እና ፋይናንስን መሠረት ያደረገ ነው። ከንግድና የውጭ ኢንቨስትመንት አንፃር የዓለም አቀፉ መቀዛቀዝ፣ እንዲሁም የቻይና ኢኮኖሚ ፍላጎት መቀነስ፣ በሸቀጦች ዋጋ መውደቅ ምክንያት የግብዓት ላኪዎችን ጎድቷል።
በሙሉጌታ በላይ
2022-06-15
