ሀገሬ ቲቪ

ፕሮፌሽናሎቹ የጩኸት አርቲስቶች

አንዳንዴ እንዲህም እንጀራ ይበላል እንዴ የሚያሰኙ ነገሮችን እንሰማለን። የሰው ልጅ ለሚከውናቸው ሁሉም ነገሮች በቦታው ችሎታ ያላቸው ወይንም ፕሮፌሽናሎችን ይፈልጋል።

አንዳንዶቹ ታዲያ አሁን ለዚህ የምን ባለሙያ ያስፈልገዋል ያሰኛሉ። እንግዲህ ዛሬ ከወደ ፊልሙ ዓለም ልንወስዳችሁ ነው። እስከ ዛሬ ስንመለከታቸው በነበሩ የምዕራባውያን ፊልሞች ላይ አደጋ ያለበትን የፊልም ክፍል እራሳቸው ተዋናዮቹ እንደማይተውኑት እናውቃለን። ከአንዳንዶቹ በስተቀር ማለት ነው፤ የራሳቸው ተተኪ ወይም በራሳቸው በነጮቹ አጠራር ስታንት ማን ተብለው የሚጠሩት ናቸው ከመኪና መኪና የሚዘሉት፣ ከፎቆች ላይ የሚወረወሩት ሻገር ሲልም በእሳት የሚለበለቡት።

ታዲያ ይህኛው ወይ ጉድ አሰኝቶን ሳያበቃ በምዕራባውያኑ ፊልሞች ላይ የምንሰማቸው የድንጋጤም ሆነ ሌሎች ጩኸቶች የራሳቸው ባለ ሙያ አላቸው መባሉን ሰማን። እነዚህ የጩኸት አርቲስቶች በፊልሞች ላይ ተዋናዮቹ የሚጮኹትን ጩኸት ተክተው እሪታቸውን የሚያስነኩ ናቸው።

እነዚህ የጩኸት አርቲስቶች ለእዚያ የፊልም ክፍል ልክክ ያለ ጩኸትን ለማምጣት ሰዓታትን በድምፅ ስቱዲዮዎች ውስጥ ያሳልፋሉ። እነዚህ አርቲስቶች በቀረፃ ወቅት ለአደገኛ ትዕይንቶች አርቲስቶች በሚያወጡት ድምፅ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ተክተው ያገለግላሉ ነው የተባለው።

አሽሊ ፔልደን የእዚህ ጥበብ ባለቤትነች። በበርካታ ፊልሞች ላይ በጩኸት አርቲስትነት ተሳትፋለች። ይህችው የጩኸት ጥበበኛ የጩኸት ክህሎቷን በለጋ እድሜዋ እንዳገኘችው ትናገራለች።

በ7 ዓመቷ የደረሰባትን በደል ለመግለፅ ድምጿን ከፍ አድርጋ ትጮኻለች ይህ ጩኸቷ ታዲያ በግዜው በነበረ አንድ ፊልም ላይ የመጮህ እድልን አስገኝቶላታል። አሽሊ እድሜዋ 20ዎቹን ሲሻገር ከ40 በላይ በሆኑ ፊልሞች እና የቴቪዥን ድራማዎች ላይ በጩኸት አርቲስትነት ተሳትፋለች።

አርቲስቶች ወዲያውኑ የሚፈለገውን ጩኸት ለመጮኽ ግዜው ላይኖራቸው አልያም የድምጽ ስፋት ላይፈቅድ ይችላል ይላል ሌላኛው የጩኸት ባለሙያ። ታዲያ ይህ አይነት ጩኸት በልምምድ እንደማይመጣ ይናገራሉ፤ ጩኸቱ ተፈጥሯዊ ነው መሆን አለበት እና በስቱዲዮ ውስጥ ሲገኙ እዛው ድርጊቱን ተከትለው ለመጮኽ እንደሚሞክሩ ይናገራሉ።

እንደ ፍርሃት ፣ ቁጣ ፣ የደስታ እና የስኬት ጩኸቶች ፣ እንዲሁም ዋይታ ፣ የስቃይ እና የድካም ጩኸቶች የተባሉ የተለያዩ ጩኸቶች አሉ። ሁሉንም ግን ሀዘን አንድ ያደርጋቸዋል።

ጩኸት እንጀራ ሆኗቸው የእለት ጉርሳቸውን ጮኸው የሚጋግሩት እነዚህ የጩኸት አርቲስቶች ስራችንን እወቁት ብለዋል።

በሳምሶን ገድሉ
2022-06-15