በ18ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቤንጃሚን ፍራንክሊን ብዙም እውቅ ያልነበረው ኤለክትሪሲቲን ማጥናት ላይ ተስቧል። ፍራንክሊን የመብረቅ እና የኤለክትሪክ ዝምድናን ለማሳየትም በመብረቅ ኪት በማብረር ኤለክትሪክ ቻርጆችን ሰብስቧል። የኤለክትሪሲቲ እና መብረቅ ዝምድናን የማጥናት ሙከራውን በዛሬዋ እለት ከ270 አመታት በፊት ነበር ያደረገው። ኤለክትሪክ ጋር የተያያዙ ቁልፍ ቃላትን ፈጥሯል። መርከቦች እና ህንጻዎችን ከመብረቅ መከላከል የሚያስችለውን የመብረቅ ዘንግም ለአለም አበርክቷል።
በ1744 ሰኔ ላይ በዩናይትድ ስቴትስ የፊላደልፊያ ሰማይ ጨለምለም ማለት ጀምሯል። ዝናብ ይወርዳል። መብረቅ ያስገመግማል። የፊላደልፊያ ሰዎች በየቤታቸው ውስጥ ናቸው። አንድ ሰው ግን ጊዜው ለምርምሩ ምቹ እንደሆነ አስቧል። ይህ ሰው ቤንጃሚን ፍራንክሊን ነው። መብረቁ እያስገነገመገመ ለምርምሩ ኪት አበረረ። ከመብረቁ ኤለክትሪክ ቻርጅ ሊሰበስብ።
የመብረቅን ኤለክትሪካዊ ባህርይ ለማሳየት ሲጠብቀው የነበረው ጊዜ ሆነ።
ቀለል ያለ ኪት አዘጋጅቷል። ለኋላ ጥቅም የኤለክትሪክ ቻርጅን መሰብሰብ ከሚችል መሳሪያ እና ከመብረቁ የሚወጣውን ቻርጅ የምትስብ ቀጭን ሺቦ አድርጎ በልጁ ዊሊያም እርዳታ ሙከራውን አደረገ።
በዚህ ሙከራውም ከመብረቅ በኤለክትሪክ ቻርጅ መሰብሰቢያው ኤለክትሪሲቲን መሰብሰብ ችሏል።
በዚህም መብረቅ የኤለክትሪሲቲ ጸባይ እንዳለው ማስረዳት ችሏል። መብረቅ ኤለክትሪክ ማሳለፍ በሚችል ብረት ውስጥ ማለፍ ይችላል የሚል እሳቤውንም አረጋግጧል።
ከተሳካ የመብረቅ እና ኤለክትሪሲቲ ግንኙነት ማሳያው በኋላ ፍራንክሊን በኤለክትሪሲቲ ላይ ስራውን ቀጥሏል። የተሳካ የመብረቅ መከላከያ የመብረቅ ዘንግንም (Lightning Rod) መስራት ችሏል።
በኤለክትሪሲቲ ምርምር ዘርፍ ስሙ የሚጠቀሰው ቤንጃሚን ፍራንክሊን ውልደቱ የ17 ልጆች አባት ከነበረ የሳሙና ሰራተኛ በ1698 በአሜሪካ ቦስተን ነው። መደበኛ ትምህርትን መከታተል የቻለው እስከ 10 አመቱ ነው። ከወንድሙ ጄምስ ጋር ለማተም ስራ ረዳት ሆኖ ተሰማራ። ኋላም አታሚ ሆኗል። ወደ ፊላደልፊያ በማምራትም የተሳካለት የቢዝነስ ሰው ሆኗል። የፔንሲልቫኒያ ጋዜጣን እና መጻህፍትንም አሳትሟል።
በሳይንስ እና በህትመቱ ዘርፍ ካበረከተው በተጨማሪ ፍራንክሊን በማህበረሰባዊ እንቅስቃሴዎች ላይም ንቁ እንደነበር ይነገርለታል።
በፔንሲልቫንያ ምክር ቤት ህግ አውጭ ሆኖ ማገልገል የቻለው ፍራንክሊን በእንግሊዝ እና ፈረንሳይም ዲፕሎማት ሆኖ አገልግሏል። ከአሜሪካ መስራች አባቶች አንዱም ነው። ዩናይትድ ስቴትስን ለመፍጠር መሰረታዊ የሆኑ አራት ሰነዶች ላይ በመፈረም ብቸኛው ፖለቲከኛም ነው። በዚህም ለአሜሪካ ነጻ ሃገርነት የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል።
የአሜሪካ ሳይንሳዊ ማህበራት አባልና መስራች ነበረም። የአሜሪካ ፊሎሶፊካል ሶሳይቲም መስራች አባልም ነው።
ስኬታማ የንግድ ሰው የሆነው ፍራንክሊን በፍልስፍናዊ ጥናቶች እና መደነቆች ውይይት ላይ መሳተፉ አልቀረም።
በ1930ዎቹ እና 40ዎቹ አዲስ የመደነቅ ምንጭ በሆነው የኤለክትሪሲቲ ግኝት ላይም ትኩረቱን አድርጓል። ከሌሎች ጓደኞቹም ጋር ኤለክትሪሲቲ ላይ ምርምር ማድረግ ጀመረዋል። ኋላም የመብረቅ እና ኤለክትሪሲቲ ግንኙነትን እስከማሳየት ደርሷል።
አታሚ፣ ጸሃፊ፣ ተመራማሪ፣ ፖለቲከኛ የሆነው እና በአሜሪካ ታሪክ ከተቀዳሚ ተጠቃሽ ሰዎች አንዱ መሆን የቻለው ቤንጃሚን ፍራንክሊን በ84 አመቱ አርፏል።
ኤለክትሪሲቲነቱን ላረጋገጠው መብረቅ መከላከያውን ለአለም አበርክቶልናል።
በአብርሃም በለጠ
2022-06-15
