በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ብክለት የሰዎችን እድሜ ከሁለት ዓመት በላይ እያሳጠረ ይገኛል፡፡
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የመጀመሪያ ዓመት የዓለም ኢኮኖሚ ቀንሷል፤ ሆኖም የዓለም አቀፍ ዓመታዊ አማካኝ ብክለት (PM2.5) ከ2019 ደረጃዎች በእጅጉ አልተለወጠም፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት የአየር ጥራት መመሪያዎችን በማሟላት የአየር ብክለት በቋሚነት የሚቀንስ ከሆነ፣ በአማካኝ የመኖር ዕድሜ ላይ 2.2 ዓመት ይጨምራል ሲሉ ተመራማሪዎች በጥናታቸው አስቀምጠዋል፡፡
ይህ በህይወት የመቆያ ጊዜ ላይ ያለው ተጽእኖ ከማጨስ ፣ ከአልኮል መጠጥና ደህንነቱ ካልተረጋገጠ ውሃ ሦስት እጥፍ ፣ ከኤችአይቪ ኤድስ ስድስት እጥፍ እንዲሁም ከግጭት እና ከሽብርተኝነት 89 እጥፍ ይበልጣል፡፡
ከ97 .3 በመቶ በላይ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ የአየር ብክለት ከመጠን በላይ በሆነባቸው አካባቢዎች ይኖራል ሲል የቺካጎ ኢነርጂ ፖሊሲ ኢንስቲትዩት (EPIC) የሳተላይት መረጃውን በማካተት አደገኛ መሆኑን ገልጿል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ እና የጤና ዳይሬክተር ማርያ ኔሪ ከዚህ ቀደም ስለ ብክለቱ አሳሳቢነት ተናግረዋል። በጣም በተጠጋጋ ሁኔታ መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ በዓለም ላይ ያሉ የሕዝብ ብዛት ያላቸው ክልሎች ከዓለም የጤና ድርጅት መመሪያ ውጪ ናቸው ፡፡
የአየር ብክለት የሕዝብ አሳሳቢ የጤና ጉዳይ ቢሆንም ችላ ተብሏል፣ ችግሩን ለመፍታት የገንዘብ ድጋፍ አሁንም በቂ አይደለም ሲልም ያስጠነቅቃል፡፡
የሁሉም የዓለም ክልል ብክለት አሳሳቢ ቢሆንም ከግማሽ በላይ የሚሆነው ግን ደቡብ እስያ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ያለው ከፍተኛ የብክለት መጠን ከቀጠለ እና በይበልጥ በተበከለ ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎች በአማካይ ወደ 5 ዓመታት ያህል ህይወታቸውን እንደሚያጡ ይጠበቃል፡፡
ከ2013 ጀምሮ 44 በመቶው የዓለም ብክለት መጨመር የመጣው ከህንድ ነው ተብሏል፡፡
ልክ እንደ ደቡብ እስያ ሁሉ ማለት ይቻላል ደቡብ ምሥራቅ እስያ 99.9 በመቶ በአሁኑ ጊዜ ደህንነቱ ያልተጠበቀ የብክለት ደረጃ አላቸው ተብሎ ይታሰባል፡፡
በደቡብ ምስራቅ እስያ በጣም የተበከሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች በመንደሌይ ፣ ሃኖይ እና ጃካርታ ከተሞች ዙሪያ ባሉ ክልሎች በአማካይ ከ 3 እስከ 4 ዓመታት ዕድሜን ያጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ቻይና ፣ዩናይትድ ስቴት፣አውሮፓ እና መካከለኛው እና ምዕራብ አፍሪካ በከፍተኛ ብክለት ስማቸው ከተጠቀሱ ሀገራት ተርታ ናቸው፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት መስፈርቶችን በተሟላባቸዉ እና የብክለት ጀረጃቸዉ ዝቅተኛ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች በአማካይ ከተበከሉ አካባቢዎች ከሚኖሩ ሰዎች ከአምስት ዓመት በላይ ይኖራሉ ሲል ጥናቱ አመላክቷል፡፡
ፒኤም 2.5 ተብሎ በሚጠራው ብክለት የተነሳ እድሜ እያጠረ መሆኑን አመላክቷል፤እ.ኤ.አ በ2013 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ብክለቱን ካንሰር አምጪ በሚል መፈረጁ አይዘነጋም፡፡ ይህ አይነቱ ብክለት ወደ ሳንባ ውስጥ በመዝለቅ ወደ ደም ይገባል፡፡
ፒኤም 2.5 ተብሎ በሚጠራው ብክለት የተነሳ የሳንባ እና የልብ ህመም በህንድ የ300 ሚሊዮን ሰዎች መኖሪያ በሆኑት ኡታር ፕራዴሽ እና ቢሃር ግዛቶች በህይወት የመቆየት ዕድሜን እየቀነሰዉ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የቺካጎ ኢነርጂ ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ዘገባ እንደሚያመለክተው በአብዛኛዎቹ ቅሪተ አካላትን በማቃጠል በአጉሊ መነጽር ብቻ የሚታይ የአየር ብክለት በዓለም ዙሪያ ያለውን ህይወት ከሁለት ዓመት በላይ አሳጥሮታል፡፡
መሪ ተመራማሪ የሆኑት ክሪስታ ሃሰንኮፕፍ እና ባልደረቦቻቸው ማክሰኞ በወጣው የአየር ጥራት ዘገባ ላይ “ንጹህ አየር ለተጨማሪ የህይወት ዓመታት መልሶ ይከፍላል” ብለዋል፡፡
በፍሬህይወት ታደሰ
2022-06-15
