ሀገሬ ቲቪ

የክረምት አደጋን ለመከላከል

ሀገራችን ለ ወራት የሚቆየውን የበጋ ወቅት አስተናግዳ አሁን ክረምትን ለመቀበል ቀናቶችን እየጠበቀች ነው። በበጋ ወቅት በመዲናችን አዲስ አበባ እንዲሁም በተለያዩ የክልል ከተሞች ከሌላው ጊዜ ለየት ያለ የ እሳት አደጋዎች እንደተከሰቱ ጥናቶች ያመለክታሉ ። የክረምት ወቅት ሲገባ የ እሳት አደጋዎች የመፈጠር እድላቸው ቢቀንስም የጎርፍ አደጋዎች በከሰል ጪስ የመታፈን አደጋ እንዲሁም በ እርጥበት አማካኘነት የሚፈጠር የ ኤሌክትሪክ አደጋ ከወቅቱ ጋር ተያይዞ የመከሰት እድላቸው ከፍተኛ ነው ።

በሚመጣው የክረምት ወቅት ሀገራችን ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ልታስተናግድ እንደምትችል የብሄራዊ ሜትሮሎጂ መረጃ ያመለክታል። እኛም ከፊታችን የሚመጣውን የክረምት ወቅት ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ከወዲሁ ለመከላከል ማህበረሰቡ ምን ጥንቃቄ ማድረግ አለበት ስንል የ አደጋ ስጋት ቅነሳ ዘርፍ ሀላፊ የሆኑት አቶ ይክፈለው ወልደ መስቀልን ጠይቀናል ።

የክረምት ወቅት ሲገባ ማህበረሰባችን ባካባቢው የሚያልፈውን ጎርፍ ለቆሻሻ መጣያነት ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። ታዲያ ቆሻሻን ከ አካባቢ ለማራቅ በማሰብ የሚደረገው ይህ ያልተገባ ድርጊት አደጋን የመፍጠር አቅሙ ከፍተኛ መሆኑን የአደጋ ስጋት ቅነሳ ዘርፍ ሃላፊ የሆኑት አቶ ይክፈለው ይናገራሉ ።

የጎርፍ አደጋ በሁሉም አካባቢ የመከሰት እድል ቢኖረውም በዝቅተኛ አካባቢዎች እና በግድቦች ስፍራ የመፈጠር እድሉ ከፍተኛ እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ ።

የጎርፍ አዳጋ እንዳይከሰት ቀድመን መውሰድ ካለብን ጥንቃቄዎች መካከል ቤቶችንም ሆነ ጊዜያዊ መጠለያዎችን ስንሰራ መሰረቱን ከመሬት ከፍ ማድረግ ።መኖሪያችን በአስጊ ቦታዎች ላይ ያለ ከሆነ የተለያዩ መከላከያ ግድግዳዎቸን መገንባት እና የምድር ቤቶች ሲሰሩ በተቻለን መጠን ውኃ የማያስገቡ ጥሬ ዕቃዎችን መጠቀም የጎርፍ አደጋዎችን ለመቋቋም እንደሚያስችሉ ባለሞያዎች ይናገራሉ ።

ባለንበት ስፍራ የጎርፍ አደጋ ቢከሰት በፍጥነት ወደ ከፍተኛ ቦታዎች መውጣት ይህ ካልተቻለም የቤቶች ጣራ ላይ በመውጣት እርዳታ ለማግኘት መሞከር ። የኤሌክትሪክ፣ የውሃ እና የጋዝ መተላለፊያ መስመሮችን እርጥበት ባልነካው እጅ ከቆጣሪ በመዝጋት በፍጥነት ከ አካባቢያቸው መራቅ ።

በፍሰት ላይ ያለ የጎርፍ ውሃን በእግር ለማቋረጥ አለመሞከር። አደጋው የደረሰበት አካባቢ ያሉ ትልልቅ ህንጽዎች መሰረታቸው ሊናጋ ስለሚችል ለተወሰነ ሰዐታት ከ አካባቢያቸው መራቅ ተገቢ መሆኑን የድንገተኛ አደጋ ባለሞያዎች ያስገነዝባሉ። ባሉበት አካባቢም አደጋ ቢከሰት በድርጅቱ ስልክ ቁጥሮች በመደወል ፈጣን እርዳታ ማግኘት እንደሚችሉ አቶ ይክፈለው ጠቁመዋል ።

ሌላኛው ከክረምቱ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ቅዝቃዜ ለመከላከል ጨሶ ያላለቀን ከሰል ወደ ቤት ማስገባት እስከሞት የሚያደርስ ከባድ አደጋን ይፈጥራል ። በመሆኑም ያቀጣጠልነው ከሰል ጨሶ እስኪያልቅ አየር ልይ ማስቀመጥ ወደቤት ካስገባን በኋላም መስኮትና በር በመክፈት አየር እንዲገባ ማድረግ አደጋው እንዳይፈጠር ያደርጋል ።

በዮሴፍ ከበደ
2022-06-20