ናዱል በ2017 በዓለም ስደተኞች ቀንን ምክንያት በማድረግ ወደ ኢትዮጵያ ገብታለች፡፡
“እኔ ወደ እዚህ የመጣሁት በትውልድ ሀገሬ ደቡብ ሱዳን በነበረው ግጭት የተነሳ ነው ፤ያው እንደስደተኛ በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ነው የምኖረው ከቤተሰቦቼ ጋር በሰላም እየኖርኩ ነው፡፡ ትምህርቴንም እንደነገሩ እየተከታተልኩ ነው ወደፊት ዶክተር አልያም ነርስ መሆን እፈልጋለሁ፡፡ እናም የተሻለ የትምህርት እድል ባገኝ ደስ ይለኛል፡፡”
በኢትጵያም በጋንቤላ ክልል ብቻ እንኳን ብንመለከት 400 ሺሕ የሚጠጉ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ይገኛሉ፡፡እንደ ናዱል አይነት በርካታ ዜጎች በኢትዮጵያም ይሁን በሌሎች ሀገራት ጥገኛ በመሆን በስደተኛ ጣቢያ ውስጥ ይኖራሉ፡፡
ይህንን ማንሳታችን እንዲየው በዋዛ አይደለም እለቱን በተመለከተ እንጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰኔ 13 የዓለም ስደተኞች ቀን ይከበራል፡፡ የዓለም የስደተኞች ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋቋመው ሰኔ 13 ቀን 1993 ዓ.ም ነበር፤ በእለቱ በ1943 ዓ.ም የተመሰረተው የተባበሩት መንግሥታት 50ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በማስመልከት የስደተኞች ስምምነትን ጨምሯል፡፡ ቀኑ ቀደም ሲል ‹‹የአፍሪካ የስደተኞች ቀን›› ተብሎ ይጠራ የነበረ ሲሆን መንግሥታቱ ድርጅት ቀኑን ‹‹የዓለም የስደተኞች ቀን›› ብሎ ሰይሞታል፡፡
በዚህ ዓመት የዓለም የስደተኞች ቀን መሪ ሃሳብ ደህንነትን የመፈለግ መብት ላይ ያተኩራል፤ ጭብጡ “ማንም፣ ምንም ይሁን፣ መቼም” ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ደህንነትቱ የመጠየቅ መብት አለው፡፡የትኛውም ስደተኛ የትውልድ ቦታው፣ዘር እና ሀይማኖቱ ሳይለይ እንኳን ደህና መጣህ ተብሎ በክብር ሊስተናገድ ይገባል ማለት ነው በሚል ይብራራል፡፡
በሚገርም ሁኔታ 83 በመቶ የሚሆኑ ስደተኞች በታዳጊ ሀገራት ተጠልለዋል፤ከ40 በመቶ በላይ የሚሆኑ የዓለም ስደተኞች ደግሞ ህጻናት ናቸው፡፡ በ2012 ዓ.ም በወጣ መረጃ በኢትዮጵያ ከ735 ሺሕ በላይ የውጭ ስደተኞች እንደሚኖሩ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
እነዚህ ስደተኞች 26 ሀገራትን መቱ ሲሆን አብዛኛው ከጎረቤት ሀገራት የሚሰደዱ ናቸው፡፡ሌላኛው በኢትዮጵያ ስደተኛ ጣቢያ የሚኖረው የደቡብ ሱዳን ተማሪ ናሂል ጆክም በተመሳሳይ ከደቡብ ሱዳን በግጭት በምክንያት በስደተኛ መጠለያ ውስጥ እንዲኖር ተገዷል፡፡
“በጣም ከባድ የሆኑ አስፈሪ ጊዜያቶችን አይቻለው ለአብነትም ለሦስት ቀናት በባዶ እግር መጎዝ ይሄ ለኔ በጣም ከባድ የሆነ ልምድ ነው፡፡በጭራሽ ሌላ ሀገር ሄጄ አላውቅም ይሄ የመጀመሪያዬ ነው በጣም አስቸጋሪነው በተለይ ስደተኛ ሆኖ ሌላ ሀገር መኖር፡፡”
ከጠቅላላው የዓለም ስደተኞች ቁጥር ከሁለት ሦስተኛው በላይ ከአምስት ሀገራት ሶሪያ፣ ቬንዙዌላ፣ ደቡብ ሱዳን፣ አፍጋኒስታን እና ማይናማር ተሰደዋል፤72 በመቶ ያህሉ ስደተኞች ወደ ጎረቤት ሀገራት ይሰደዳሉ፡፡ ከእነዚህ ሀገራት መካከል በሆነችው ደቡብ ሱዳን በግጭት ምክንያት ዛሬም ዜጎች መሰደዳቸውን አላቆሙም፡፡
“ለዓለም የማስተላልፈው መልዕክት ቢኖር ልክ እንደ ደቡብ ሱዳን ከሀገራቸው ከቤታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ህይወት ማሻሻል ቢቻል እላለሁ፡፡ ወደፊት ይህንን ለመቅረፍ እሰራለሁ፡፡ ህልሜ ሀገሬን ከዚህ ችግር በማውጣት መቀየር እፈልጋለሁ፡፡”
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አሀዛዊ መረጃ መሰረት ቱርክ ከፍተኛውን ስደተኞችን የምታስተናግድ ሀገር ስትሆን 3.6 ሚሊዮን ስደተኞች ይኖሩባታክ፤ ተከትላ ኮሎምቢያ በ1.8 ሚሊዮን ስደተኞች በመያዝ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ እለቱ ሰላምን ለማስፈን እና ለግዳጅ መፈናቀል መፍትሄ ተጨማሪ እርምጃዎችን ለመውሰድ ‹‹እንደ ማንቂያ ጥሪ›› መሆን አለበት ብለዋል፡፡
በዩክሬን ጦርነት እና በሌሎች ገዳይ ግጭቶች ምክንያት ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ታሪክ ከፍተኛው የስደተኞች ቁጥር ተመዝግቧል፡፡
“በሪፖርታችን እንደገለጽነው በመላው ዓለም ከ100 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተሰደዋል አሊያም በግዴታ ተፈናቅለዋል፤ ቤታቸውንም ለቀዋል ለምን ቢሉ በጦርነት፣ ግጭት፣ ብጥብጥ፣ የሰብአዊ መብት ረገጣ፣መገለል እና በሌሎችንም ምክንያቶች፡፡ይህ የምንኖርበት ዓለም በጣም አስፈሪ ምልክት ነው፡፡”
ከ6 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች በስደት፣ በጦርነት ወይም በአመጽ ምክንያት ቤታቸውን ለቀው ለተሰደዱ ሰዎች አፋጣኝ ጥበቃ እና እርዳታ በሚሰጡ ካምፖች ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ከዓለም ትልቁ የስደተኞች ካምፕ የሆነው የኬንያው ዳዳብ ከ329 ሺሕ በላይ ስደተኞችን ይዟል፡፡
በፍሬህይወት ታደሰ
2022-06-20
