ምግብ ለሰው ልጅ ቆሞ የመሄዱ ዋስትና፣ ህያው ሆኖ እንዲኖር የሚያደርግ አስፈላጊ ነገር ነው። ታዲያ የምንበላው ምግብ በሰውነታችን ውስጥ ገብቶ እንዲስምማ መምረጥ የእኛው የሰዎች ፈንታ ነው።
እንደ ለጨዋታ ወደሆዳችን የምናስገባቸው ነገሮች በኋላ መዘዛቸው ቀላል የሚባል አይደለም። ይህንን ሁሉ ማለታችን ያለምክኛት አይደለም። በአንድ ወደ ጉልምስናው በተጠጋ ሰው ሆድ ውስጥ 233 ሳንቶሞች እና ሌሎች ባዕድ ነገሮች ተገኙ መባሉን ብንሰማ ነው።
ነገሩ የሆነው ከወደ ቱርክ ነው። የኢፔኪዮሉ ሰው ስሙ ቡርሃን ዴሚር ይባላል። 35 ዓመቱ ነው። ታዲያ ይህ ሰው በቅርቡ ከፍ ያለ የሆድ ህመም ይሰማው ጀምሯል። ነገሩ ያሳሰበው ወንድሙ ቡርሃንን ወደ ሆስፒታል ይዞት ይሄዳል።
ሃኪሞቹ የቡርሃንን የሆድ ህመም መንሳኤ ፍለጋ ሲዳክሩ ቆይተው ኋላ ላይ በአልትራሳውንድ እንዲታል ያደርጉታል። የኤክስሬይ ምርመራም አልቀረውም። ዶክርተሮች ያዩትን ማመን አልቻሉም፤ በርከት ያሉ ባዕድ ነገሮች በጨጓራው እና በትልቁ አንጀቱ ውስጥ ተደላድለው ተቀምጠዋል።
ሃኪሞቹ ለቡርሃን የቀዶ ህክምናን አድርገው ቁሶቹን ከሆዱ አውጥተውለታል። ቡርሃን የቱርኩን መገበያያ ገንዘብ አንድ ሊሬ ሳንቲሞች፣ ባትሪዎች፣ ማግኔቶች፣ ጥፍር መቁረጫዎች፣ የመስታወት ቁርጥራጮች፣ ድንጋዮች እና ብሎኖች በምቾት ኑሯቸውን አድርገውበት ነበር።
ሃኪሞቹ ለግዜው የለዩዋቸውን ቁሶች በስም ያለዩዋቸውን ደግሞ በእንግሊዝኛው Z ፊደል ሰይመዋቸዋል። ታዲያ የቡርሃንን ሆድ ጋራጅ ነበር ወይ ያሰኙት ቁሶች እንዴት በቡርሃን አፍ አልፈው በትልቁ አንጀቱ ውስጥ ሊገኙ እንደቻሉ የተባለ ነገር የለም።
ለግለሰቡ የቀዶ ህክምና ከሰጡት ሀኪሞች መሀከል አንደኛው እንዲህ አለ፤ አስቀድመን በጨጓራ ግድግዳ ላይ ሁለት ሚስማሮችን ብቻ ነበር ያየነው በኋላ ግን በትልቁ አንጀቱ ውስጥ በርካታ ሳንቲሞች እና እንደ ባትሪ ድንጋይ ያሉ ቁሶችን ልናወጥ ችለናል። ታዲያ ሀኪሞቹ ከቡርሃን ሆድ ውስጥ ሁሉንም ባዕድ ነገሮች አውጥተው ጽድት አድርገውለታል።
ቡርሃንም አሁን በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛል። ሃኪሞቹ እንዳሉት ከሆነ እንዲህ አይነቱ ነገር ምን አልባት በሕፃናት ላይ ቢከሰት እንጂ እራሱን በሚያውቅ ትልቅ ሰው ላይ እምብዛም አይስተዋልም።
ከዚህ ቀደም ልክ እንደ ቡርሃን ሁሉ ከ10 የሚበልጡ ሚስማሮችን እና ከ260 በላይ ሳንቲሞችን ውጦ የነበረ ሰው ህክምና ማግኘቱ ይታወሳል። ሌሎችም እንዲሁ በሆዳቸው ውስጥ አሸን ሳንቲሞች እና የብረት መዓት የተገኘባቸው ሰዎች ስለመኖራቸው ተመዝግቦ ይገኛል።
በሳምሶን ገድሉ
2022-06-20
