በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሚዥንጋ ወረዳ ሴነ ቀበሌ ውስጥ በሚገኙ መንደሮች በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው የሸኔ ታጣቂ ቡድን በቦታው ይኖሩ በነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ አሰቃቂ ግድያ መፈጸሙን በዚህም ጥቃት በብዛት ሴቶች እና ህጻናት መሞታቸውን ኢሰመጉ ባገኘሁት መረጃ አረጋግጫለሁ ብሏል።
ከተጎጂዎች መካከልም ጥቃቱን በመሸሽ መስጊድ ውስጥ ገብተው በነበሩ ሰዎች ላይም ጥቃት ተፈጽሞ በርካታ ሰዎች መገደላቸው ጥቃቱ በጣም አሰቃቂ እና የጭካኔ ድርጊት መሆኑን በመግልጽ የአካል ጉዳት፣ እገታና ንብረት ውድመት መከሰቱን፣ ይህንንም ጥቃት በመሸሽ በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን ለማትረፍ በየጫካው ተበታትነው እንደሚገኙ፣ ብዙ ቁጥር ያላቸው አስክሬኖች በአንድ አካባቢ ላይ በጅምላ እንደተቀበሩ ዛሬ ባወጣው አስቸኳይ መግለጫ ገልጿል።
በዚህ ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን እና ከሟቾች ውስጥ ብዙውን ቁጥር የሚይዙት ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውን በአካባቢው የሚገኙ መኖሪያ ቤቶች በእሳት መቃጠለቸውን እና ጥቃቱ ከባድ መሳሪያ ጭምር በመጠቀም የተፈጸመ መሆኑን ገልጿል።
ከሁሉ በላይ ጉዳዩን አሳዛኝ የሚያደርገው ይላል በመግለጫው አፋጣኝ የሆነ እርምጃ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተወሰደ ባለመሆኑ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት፣ አካል ጉዳት እና ንብረት ውድመት ምክንያት ሆኗል።
በተጨማሪም በአካባቢው የመንግሥት የጸጥታ ኃይል የተሰማራ ቢሆንም ተጨማሪ ኃይል በወረዳው በሚገኙ ቀበሌዎች ላይ ካልተሰማራ እና የሰዎችን ደህንነት ካልጠበቀ ተጨማሪ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል ኢሰመጉ ከአካባቢው ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለመረዳት ችያለዉ ብሏል።
በታጣቂዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶችን መንግሥት መፍትሄን እንዲያበጅ በተደጋጋሚ ጥሪ ባቀርብም የፌደራል መንግስት እንዲሁም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ለጉዳዩ ተገቢውን በቂ ትኩረት ባለመስጠቱ እና ጥቃት አድራሾች ላይ ህጋዊ ተጠያቂነትን ባለመመስረቱ ይህ ዘግናኝ ድርጊት ለመፈጠሩ ምክንያት መሆኑን ለመረዳት ችለያለዉም ብሏል።
በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል ነቀምቴ አካባቢ በሸኔ ታጣቂ ቡድን እና በመንግሥት የጸጥታ አካላት በሚወሰዱ እርምጃዎች በርካታ ቁጥር ያላቸው ንጹሀን ሰዎች ላይ ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ ንብረት ውድመት እና ሌሎችም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆኑን እንዲሁም በመንግሥት የጸጥታ አካላት ከሸኔ ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ላይ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆኑ እስራቶች እየተፈጸሙ መሆኑን ለመረዳት ችያለሁ ብሏል።
በዚህም መሰረት የፌደራል መንግሥት እና የሚመለከታቸው የክልል መንግሥታት የዜጎችን ደህንነት የማስከበር ተቀዳሚ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቋል።
በአካባቢው ከሸኔ ጋር በሚደረጉ ውጊያዎች ሁለቱም ወገኖች በምንም ሁኔታ በግጭቱ ቀጥተኛ ተሳትፎ የማያደርጉ ሰዎችን ከማጥቃት እንዲቆጠቡም ጥሪ አስተላልፏል።
በተደጋጋሚ በአከባቢው የሚደርሱ የሰበዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በመቆጣጠር የአካባቢውን ሰላም እንዲያረጋግጥ፣ በዚህ ጥቃት ላይ ተሳትፎ ያላቸውን ማንኛውንም አካላት ተገቢውን ምርመራ በማድረግ በሕግ ተጠያቂ እንዲያደርግ እንዲሁም በአካባቢው በቂ የጸጥታ አካላትን በማሰማራት መሰል ጥቃቶች ዳግም እንዳይፈጸሙ እንዲከላከል ጠይቋል።
የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የማሕበረሰብ አንቂዎች፣ ሲቪክ ማህበራት እና የሚመለከታቸው ሁሉ መንግሥት የዜጎችን ደህንነት የማስከበርኃላፊነቱን በቂ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ውትወታ በማድረግ የበኩላቸውን ኃ ላፊነት እንዲወጡ ጥሪውን ያቀረበ ሲሆን ተጨማሪ የምርመራ ስራን በማከናወን ሰፋ ያለ ዘገባን አዘጋጃለሁ ብሏል።
በፍሬህይወት ታደሰ
2022-06-21
