ከህልውና ዘመቻው ጋር በተያያዘ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ተገቢውን እንክብካቤ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ። ይህን ያሉት በጤና ሚኒስቴር የሴቶች፣ ህጻናት እና አካል ጉዳተኞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ፋጡማ ሰይድ ናቸው። ዛሬ በተካሄደው የጸረ ጾታዊ ጥቃት ወይም የነጭ ሪባን ማጠቃለያ ዝግጅት ላይ ወይዘሮ ፋጡማ በሃገራችን የህልውና ዘመቻው እየተደረገባቸው ባሉ አካባቢዎች ብዙ ሴቶች ጥቃት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል። ወይዘሮ ፋጡማ ለእነዚህ ጥቃት ለደረሰባቸውን ሴቶች ተገቢውን እንክብካቤ ለማድረግ በፌደራል ደረጃ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል። በአለም ለ25ተኛ ጊዜ በሃገራችን ደግሞ ለ16ተኛ ጊዜ የጸረ ጾታዊ ጥቃት ወይም የነጭ ሪባን ቀን ዘመቻ ለ16 ቀናት ከህዳር 15 እስከ ህዳር 30 ሲካሄድ ቆይቷል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህጻናት እና ማህበራዊ ዘርፍ ከኢንጀንደር ሄልዝ ጋር በመተባበር የጸረ ጾታዊ ጥቃት ዘመቻ ማጠቃሊያ የፓናል ውይይት አካሂዷል። በማጠቃለያ ዝግጂቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህጻናት እና ማህበራዊ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሃላፊ እና የሴቶች ዘርፍ ሃላፊ የሆኑት ወይዘሮ ሜሮን አረጋዊ የጸረ ጾታዊ ጥቃት ዘመቻ በ16 ቀናት የሚወሰን ሳይሆን አመቱን ሙሉ ስራ የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል። ሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ማህበራዊ ቀውስ የሚፈጥሩ እና የሴቶችንም ምርታማነት የሚቀንሱ መሆናቸውን ሃላፊዋ ገልጸዋል።
በሀገሬ ቲቪ
2021-12-10
