ሀገሬ ቲቪ

“የበጀት ጉድለቱ የዋጋ ግሽበቱን እና የሥራአጥ ቁጥሩን ሊጨምር ይችላል”

ኢትዮጵያ ለ2015 በጀት ዓመት ከሌሎች ዓመታት በተለየ ከፍያለ ነው የተባለለትን በጀት መድባለች። 786 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር። ይኹን እንጂ መንግሥት 231 ነጥብ4 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት ያጋጥመኛል ብሏል ይኽን የበጅት ጉድለት ታዲያ 224ነጥብ5 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ በሚገኝ ገንዘብ ለመሙላት ፤ 6ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ድግሞ ከውጪ አገር ለመበደር አቅጃለሁ ማለቱ ይታወሳል።

ለመኾኑ የመንግሥት የበጀት ጉድለቱን በዚኽ ዓይነት ዕቅድ የመሙላቱ ዕቅድ እንዴት ይታያል። በሀገሪቱ ምጣኔሀብት ኾነ በሕዝቡ የዕለተለት ኑሮ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ይኖር ወይ ስንል የምጣኔሀብት ባለሙያዎችን አናግረናል።

አቶ ተስፋዬ ኃ/ሚካኤል የብሔራዊ ባንክ የአክሲዮን ገበያ አማካሪ ናቸው። የበጀት ጉድለት በሀገሪቱ ያለውን የዋጋ ንረት ሊያባብስ የሚችል መኾኑን በመግለጽ መንግስት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች መለየት እንዳላበት ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ የበጀት ጉድለቱን ለመሙላት ከሀገርውስጥ እና ከውጪ ብድር የመውሰድ እርምጃ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳለ የነገሩን ደግሞ የምጣኔሀብት ባለሙያ የኾኑት ዶ/ር አረጋ ሹመቴ ናቸው።

መንግሥት ከነዚኽ የመፍትሔ እርምጃዎች በተጨማሪ የጎደለውን በጀት ለመሙላት ሊወስደው ስለሚችለው ሌላ አማራጭ የገንዝብ ኀትመት ሊኾን እንደሚችል ዶ/ር አረጋ ተናግረዋል መንግሥት ተቸማሪ ገንዘብ በማተም የበጀት ጉድለቱን ለመሙላት ከሞከረ ከፍተኛ የኾነ የዋጋ ንረት እና ሥራ እጥነት ሊከሰት እንደሚችል ተናግረዋል።

በሙሉጌታ በላይ
2022-06-22