በአውሮፓውያኑ ፈር ቀዳጅነት ሚሊዮኖች አፍሪካውያን በባርነት ስም የአትላንቲክ ውቅያኖስን በግፍ እንዲያቋርጡ ተገደዋል። በዚያ የሰው ልጅ የታሪክ ጠባሳ የሰው ልጅ ክብር ከእንስሳትም በሚያንስ አያያዝ ጎድፏል። ከዚህ ጋር በተያያዘ እለቱን ከታሪክ አንድ አትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ የተከናወነ ታሪክን ሊያስቃኘን ወደ 1775 መለስ ይላል።
ባሪያ በሚለው የሰው ልጆች እሳቤ ሰው ሰው አይደለም። ወደ 18ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በታሪክ ሃዲድ መለስ ስንል በ1775 አንዲት በምርኮ ባሪያ ተብለው የተሰየሙ ሰዎችን የያዘች ዞንግ የተሰኘች የእንግሊዝ መርከብ አትላንቲክ ላይ በጉዞ ላይ ነች። የዞንግ ሰራተኞች በትንሹ 142 የሚደርሱትን ባሪያ ብለው የሰየሟቸውን ሰዎች ወደ ውቅያኖሱ ወረወሩ።
በ1774 ዞንግ የተሰኘችው መርከብ 442 ለባርነት የታጩ አፍሪካውያንን ይዛ መነሻዋን ከጋና አክራ አድርጋለች። ጉዞዋን ወደ የቅኝ ግዛት እርሻ ወደ ‘ሚከናወንበት ደቡብ አሜሪካ ጀማይካ አደረገች። በባሪያ ንግድ የባህር ጉዞ እንደተለመደው ሁሉ ዞንግ መርከብ መጫን ከምትችለው የሰው ቁጥር በእጥፍ ጭናለች።
የመርከቧ የውሃ ላይ ጉዞ ዝግ ያለ ሆነ። በሰራተኞቿ የአሰሳ ስህተት ደግሞ ጉዞዋ ተራዘመ። ህጉ አይከለክላቸው አይከስሩበት ሰራተኞቹ እነዚያን ከአፍሪካ የወሰዷቸውን ሰዎች የመወርወር ሃሳብ አደረባቸው ። እንደዕቃ ሁሉ የቆጠሯቸውን ሰዎች ወደ ውቅያኖሱ ጣሏቸው። በጣሏቸው ሰዎች የከሰሩት ኪሳራቸው በእንግሊዝ ህግ ይካካሳል። አንድ ሁለት እያሉ በገፍ አፍሪካውያኑን ወረወሯቸው። ከልካይ በሌለበት ከ140 የሚልቁ ሰዎች ወደ ውቅያኖስ ተጣሉ። ኋላም መርከቧ ውሃ ላይ ከመጣል የተረፉትን ቀሪዎቹን 208 ሰዎች ይዛ ጀማይካ ደረሰች።
ቀድሞ በባርነት ይገዛ የነበረው እና ኋላም ባርነትን ተቃዋሚ የሆነው ኦላውዴ ኢኳኖ ከሌላኛው የባርነት ተቃዋሚ ግራንቫይል ሻርፕ ጋር የዞንግ መርከብ ሰራተኞች ሰዎቹን በመግደላቸው ክስ እንዲመሰረትባቸው የሚያስችል መንገድን መፈለግ ማስተባበር ጀመሩ። ግና ባሪያ ለተባሉት ሰዎች የጅምላ ግድያ ፍትህ ተነፈጋቸው።
በዛሬዋ እለት በ1775 በዞንግ መርከብ ላይ በተከናወነው ጉዳይ ላይ በእንግሊዝ ለንደን በተሰየመው ችሎት ዋና ዳኛው “ባሮችን መጣል ፈረሶችን ከመጣል ተመሳሳይ ነው” ሲሉ ተደመጡ።
በሰዎቹ ላይ የተፈጸመው የውሃ ላይ መጣል ግድያ ምንም እንኳን ፍትህ ቢነፈገውም የኦላውዴ ኢኳኖ እና ግራንቫይል ሻርፕ ታሪኩን በሰፊው ለህዝብ ማድረስ ለባርነት ተቃውሞ እንቅስቃሴ መነቃቃትን ፈጥሯል።
ከዞንግ ፍርድ ጥቂት ወራት በኋላ ዘ ሶሳይቲ ኦፍ ፍሬንድስ የጸረ ባርነት ዘመቻን ጀመረ።የባሪያ ንግድን የመቃወም ማህበር የሆነው ዘ ሶሳይቲ ኦፍ አቦሊሽን ኦፍ ስሌቭ ትሬድ የተሰኘው ማህበርም ከአራት አመታት በኋላ ተመሰረተ።
ማህበራቱ የዞንግ መርከብን ታሪክ ጎልቶ እንዲታይ ለማድረጋቸው ምስጋና ይገባውና እንቅስቃሴያቸው ፍሬ ማፍራት ችሏል። በ18ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የእንግሊዝ ፓርላማ የአትላንቲክ የባሪያ ንግድን ህገወጥ ነው አለ። ከዚያ በፊትማ ህጋዊ ነበር። በእንግሊዝ አገዛዙ ሁሉ ባርነት እንዲቀር በ1820ዎቹ ከለከልኩ አለች።
ግና ደግሞ የዞንግ መርከብ ታሪክ የአትላንቲክ የባሪያ ንግድ ገጽታ መታወሻ ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል።
በአብረሃም በለጠ
2022-06-22
