የማዕድን ሚኒስቴር የማዕድናት ፍለጋ ፈቃድ ወስደው ለረጅም ጊዜያት በገቡት ውልና አቅርበው ባፀደቁት መርሀ ግብር መሠረት መስራት ባልቻሉ ኩባንያዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን ገለጸ፡፡
ኩባንያዎቹ ሚኒስቴሩን ጨምሮ በየደረጃው ባሉ ባለድርሻዎች ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም በሚገባው መልኩ ወደ ልማት ባለመግባታቸው የ116 ኩባንያዎች የማዕድን ፍለጋ ፈቃድ መሠረዙን የማዕድን ሚኒስትሩ ኢ/ር ታከለ ኡማ ዛረ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
በተጨማሪም በማዕድናት ምርት ፈቃድ ወስደው ነገር ግን በአግባቡ አልሰሩም የተባሉ የ6 ኩባንያዎች ፈቃድ ተሰርዟል፡፡
ከወርቅ ማዕድናት ውጪ ያሉ ሌሎች ማዕድናት ወደ ውጪ ለመላክ የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ወስደው ፈቃድ የተሠጣቸው ነገር ግን፤ በህጋዊ ሽፋን በኮንትሮባንድ ንግድ ላይ ተሠማርተው የተገኙ 850 የማዕድን ላኪዎች ፈቃድ መሠረዙን ሚንስትሩ ተናግረዋል ።
በአጠቃላይ 972 በማዕድን ምርመራ ፤ ምርትና ኤክስፖርት ዙሪያ ፈቃድ የወሰዱ ኩባንያዎች ፈቃድ ተሰርዟል::
በክልሎች በኩል የተሠጡ ፈቃዶች በዚህ ወር መጨረሻ ተገምግሞ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ከሥምምነት መደረሱም ተሰምቷል፡፡
ባለፉት 11 ወራት ኢትዮጵያ ከወርቅ ምርት 513 ነጥብ 9 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘቷን የገለጹት የማዕድን ሚኒስትሩ ኢጂነር ታከለ ኡማ በዚህ ዓመት የወጪ ንግድ ማዕድናትን በሥፋት፣ በጥራት እንዲሁም በዓይነት በማምረት የተገኘው ገቢ ቡና በመላክ ከተገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠ ዘርፍ መሆኑ አብራርተዋል፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ፍቃዶችን ወስደው በገቡት ውል መሠረት ሥራቸውን ያላከናወኑ 972 በማዕድን ምርመራ ፣ ምርት እና ኤክስፖርት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሐብቶች ህዝብን በሚጎዳ ተግባር ላይ ተሠማርተው በመገኘታቸው ፍቃዳቸው እንዲቋረጥ መደረጉን ገልፀዋል፡፡
የማዕድን ሚኒስቴር ኢትዮጵያ እና ዜጎቿ ከማዕድንና ተፈጥሮ ሐብቶች የሚገባቸውን ያህል እንዲጠቀሙ የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡
የማዕድን ዘርፉ የተለያዩ ሀገራዊ አካባቢያዊ ፈታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ በላቀ ትጋት እየተንቀሳቀሰ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚጠይቁ የማዕድን ኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት የተከናወኑ ሥራዎች ተሥፋ ሰጪ ውጤቶችን እያስመዘገቡ መሆኑንም ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ላይ አመላክተዋል፡፡
በፍሬህይወት ታደሰ
2022-06-22
