በአፍጋኒስታን በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ ወደ 300 የሚጠጉ ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ ከ200 በላይ ሰዎች ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው የ አገሪቱ የ አደጋ መከላከያ ባለስልጣን አስታውቋል ።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለ ሥልጣን የሆኑት ሳላሁዲን አዩብ አደጋው የተከሰተበት ቦታ በተራሮች የተሸፈነ በመሆኑ የሟቾችን ቁጥር ለመገመት አዳጋች ሆኖብናል ያሉ ሲሆን ነገር ግን የሟቾች ቁጥር ከ 300 ሊበልጥ እንደሚችል ጠቁመዋል ።
የመሬት መንቀጥቀጡ 6.1 በሆነ መጠን 51 ኪሎ ሜትር ጥልቀት ላይ የደረሰ አደጋ እንደነበር ተመራማሪዎች ገልጸዋል ።
ሄሊኮፕተሮች ተጎጂዎችን ከአደጋዉ ስፍራ ወደ ሆስፒታል ሲያመላልሱ ቆይተዋል፡፡ ባክታር የተሰኘ የዜና አገልግሎት በበኩሉ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል የዘገበ ሲሆን ከ600 በላይ ሰዎች በአደጋዉ ቆስለዋል ብሏል። የመሬት መንቀጥቀጡ የተከሰተው ከደቡብ ምስራቅ ክሆስት ከተማ 44 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ነበር፡፡
ኢቲላት-ኢ ሮዝ የተሰኘው የሀገሪቱ የቴሌቭዥን ጣቢያ በአደጋው አንድ ሙሉ መንደር መውደሙን አስታውቋል ። ከአፍጋኒስታን በተመጨማሪ በፓኪስታን እና ህንድ ከ500 ኪሎ ሜትር በላይ የመሬት መንቀጥቀጡ እንዳጋጠመ መረጃዎች የወጡ ሲሆን በሰው ህይወት ላይ ስለደረሰ ጉዳት እስካሁን የተገኘ መረጃ ባይኖርም የመሬት መንቀጥቀጡ በፓኪስታን ትንሽ ጉዳት አድርሷል ተብሏል ።
አፍጋኒስታን ባለፉት 10 አመታት በደረሰባት የመሬት መንቀጥቀጥ ከ7,000 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን በየዐመቱ በአማካይ 560 ሰዎች በመሬት መቀጥቀጥ እንደሚሞቱ የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ያወጣው መረጃ ያመላክታል ።
በጋዜጠኛ እና የፖለቲካ ጸሃፊ የሆኑት ሄዳያቱላህ ፓኪን በሀገሪቱ የሚገኙ አብዛኞቹ ቤቶች የተገነቡት በአፈር ፣እና በሌሎች ጥቃቅን ቁሶች ነው ። ለዚህም ምክንያቱ አፍጋኒስታን ለ አመታት ባላባራ ግጭት ውስጥ መግባትዋ ነው ይላሉ ። የሀገሪቱ መሰረተ ልማቶች ተጠናክሮ አለመሰራት አፍጋኒስታንን ለተፈጥሮ አደጋዎች ተጋላጭ አድርጓታል ሲሉም አክለዋል ። አሁንም ለ ሀገሪቱ የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶች ካልተሟሉ እንዲሁም ያሉት ህንጻዎች እድሳት ተደርጎ መሰረታቸው ካልተጠናከረ አፍጋኒስታን በቀላሉ በተፈጥሮ አደጋዎች መመታትዋ አይቀርሬ ነው ሲሉ ስጋታቸውን ይናገራሉ ።
በዮሴፍ ከበደ
2022-06-22
