ሀገሬ ቲቪ

63 ሺሕ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የማስረከብ ዕቅድ

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ከ63 ሺሕ በላይ የጋራ ቤቶችን በሚቀጥለው ወር አስረክባለሁ አለ፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት በተካሄደው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ የወጣላቸውና ያልተረኩቡ ናቸው፡፡ በ16 ሳይቶች የሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤት መሆናቸውን ሪፖርተር ዘግቧል፡፡ የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አውራሪስ ከበደ፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ላይ ቅድመ ርክክብ ቢደረግም፣ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ባለመጠናቀቃቸው የቤት ባለቤቶች ሙሉ ለሙሉ ተረክበውና አፅድተው አለመግባታቸውን አስታውሰዋል፡፡ እነዚህ የቤት ባለቤቶችበ13ተኛው ዙር የ20/80 ዕጣ፣ በሁለተኛው ዙር የ40/80 ዕጣ፣ እንዲሁም እንደ የልማት ተነሺነት ባሉ ልዩ ልዩ ምክንያቶች የቤት ባለቤት የሆኑ ናቸው፡፡ በ2011 በወጣው ዕጣ 52 ሺሕ ቤቶች ለባለዕድለኞች የተሰጡ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 47 ሺሕ የሚሆኑት የቤት ባለቤቶች ውል መፈጽማቸው ተገልጿል፡፡ ነዋሪዎቹ ቤቶቹን ላለመረከባቸው ምክንያት የሆነው ቤቶቹ ሙሉ ለሙሉ ተገንብተው አለማለቃቸው ብቻ ሳይሆን እንደ ውኃ፣ መብራትና መንገድ ያሉ የመሠረተ ልማት አቅርቦቶች አለመዘርጋታቸው እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ በተጨማሪም የነዋሪዎቹን የቤት መረከቢያ ጊዜ ያስረዘሙ ምክንያቶች ለብዙ ጊዜያት የተከማቹ ናቸው የተባለ ሲሆን፣ የፕሮጀክት አፈጻጸም ማነስ፣ ፋይናንስ እጥረትና ከመሠረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት ጋር በቅንጅት አለመሥራት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በሀገሬ ቲቪ
2021-12-13