ሀገሬ ቲቪ

የቡድን 7 ሀገራት አዲስ ዕቅድ ይፋ አደረጉ

በደቡባዊ ጀርመን በሽሎስ ኤልማ ዓመታዊ ስብሰባቸውን ያደረጉት የቡድን ሰባቶቹ ሀገራት በድህነት የሚማቅቀው ዓለም በቻይና እግር ሥር ወድቋል እያሉ ነው።

ለዚህም ይመስላል 600 ቢሊዮን ዶላር ደሃ ሀገራት የመሰረተ ልማት ግንባታ ለማዋል መዘጋጀታቸውን ያስታወቁት። ይህንን እቅዳቸውን “ሽርክና ለአለም አቀፍ መሠረተ ልማት እና ኢንቨስትመንት” ሲሉም ጠርተውታል።

ቻይና በአፍሪካ እና ሌሎች ድሃ የዓለማችን ሀገራት የጀመረችውን የቤልት ኤንድ ሮድ ባለ ብዙ ትሪሊዮን ፕሮጀክት ለመከላከል ያለመ ስለመሆኑም ነው የተሰማው።

እነዚህ የዓለማችን ፈላጭ ቆራጭ ሀገራት ከሩሲያ ጋር የገቡበት ፍጥጫ አሁን ከቻይናም ጋር ለመድገም ዳር ዳር እያሉ ይመስላል። በተለይ አፍሪካ በቻይና የመሰረተ ልማቶች መረብ ውስጥ መውደቋ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ስጋቶችን የደቀነባቸው ይመስላል።

በዲሞክራሲ ሰበብ እንዳሻቸው በአፍሪካ ምድር ሲዘሉ ለነበሩት ምዕራባውያኑ አሁን የመጫወቻ ካርዱ ከእጃቸው አፈትልኮ በተቀናቃኞቻቸው እጅ ላይ ሳይወድቅ አልቀረም።

የልዕለ ኃያሏ ሀገር መሪ ባይደን እንዲህ ሲሉ ተደምጠዋል፤ “ይህ የሰብዓዊነት ጉዳይ አይደለም፤ ይህ ለሁላችንም የኢኮኖሚ እና የብሔራዊ አደጋ ስጋት ነው ለሁሉም ግልፅ መሆን እፈልጋለው ይህ እርዳታ ወይም ልገሳ አይደለም፣ ለሁላችንም ትርፍ የሚያመጣ ኢንቨስትመንት ነው። ከዲሞክራሲ ጋር የተባበሩትም ጥቅሙን የሚያዩበት ነው።”

ምዕራባውያኑ ሀገራት እናደርገዋለን ላሉት የመሰረተ ልማት ዕቅድ 600 ቢሊዮኑን እስከ 2019 ዓ.ም ድረስ ሰብስቦ ለመጨረስ አቅደዋል። በ2005 ዓ.ም የቻይናው መሪ ሺ ዢን ፒንግ ያስጀመሩት ይህ የቤልት ኤንድ ሮድ ፕሮጀክት የደቡብ ምስራቅ እስያን ከደቡብ እስያ፣ መካከለኛው ምስራቅን ከአፍሪካ፤ ኢንዶ-ፓሲፊክ የባህር መስመሮችን ጨምሮ ሀገራቱን ማስተሳሰርን ያለመ ነው።

በዚህም ቻይና በእነዚህ ሀገራት ውስጥ ወደቦች፣ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች፣ የባቡር ሐዲዶች፣ መንገዶች፣ ድልድዮች፣ አውሮፕላን ማረፊያዎች፣ ግድቦች፣ የድንጋይ ከሰል ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች እና የመንገድ መተላለፊያ ዋሻዎችን ከራሷ ኪስ ለሀገራቱ አበድራ ተገነባላቸዋለች።

ይህ የቻይና አካሄድ የሀገራቱን ዲሞክራትነት አልያም ሌሎች የፖሊሲ ጉዳዮችን እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚጠይቅ አይደለም። ይህ ይበርካታ ድሀ ሀገራትን ከምዕራባውያን ልባቸውን ሲሸሽ ቆይቷል።

የቡድን ሰባቶቹ ሀገራት ውሳኔም አሁን ከምፅዋት ባለፈ ድሀናቸው በሚሏቸው ሀገራት ውስጥ ወደሽ ስራ ለመሰማራት ቀበቷቸውን ጠበቅ ስለማድረጋቸው ማሳያ ተደርጎ እየተወሰደ ይገኛል።

የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ፎን ደር ሌየን ለጉባኤው እንዳሉት ቻይና እንቅስቃሴዋን በጀመረችበት 2005 ዓ.ም የህብረቱ ሀገራት ዘላቂ አማራጭ ለስጠት በማለም 300 ቢሊዮን ዩሮ (317 ቢሊዮን ዶላር) ድጋፍ ለእነዚሁ ደሀ ሀገራት አድርገው እንደነበር አንስተዋል።

አሜሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት እና የዓለምን ጤና፣ የሥርዓተ-ፆታ ፍትሃዊነትን እና የዲጂታል መሠረተ ልማትን ለማሻሻል የሚረዱ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት 200 ቢሊዮን ዶላር በእርዳታ፣ በፌዴራል ፈንድ እና በግል ኢንቨስትመንት በአምስት ዓመታት ውስጥ እንደምታደርግ ባይደን በቡድን 7 ሀገራት ጉባኤላይ ተናግረዋል።

የቻይናው መሪ ሺዢን ፒንግ በበኩላቸው ከሰሞኑ በነበረው የብሪክስ ሀገራት ጉባኤ ላይ የብሪክስ ሀገራት ለዓለም እኩልነት ሀላፊነቱን ወስደው መስራት እንደሚገባቸው መናገራቸው ይታወሳል።

በሳምሶን ገድሉ
2022-06-27