ሀገሬ ቲቪ

እለቱን ከታሪክ - የኢቦላ ቫይረስ ጅማሮ

ጊዜው 1968 ነው። በዛሬዋ እለት ታዲያ በሱዳን በንዛራ ከተማ ሱቅ ሻጭ የሆነ ሰው ታመመ። ከአምስት ቀናት በኋላም መሞቱ ተሰማ። በአፍሪካ የመጀመሪያው የተመዘገበ የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝም መስፋፋቱን ጀመረ። በጊዜው 284 ኬዞች ተመዝግበዋል። በበሽታው ከተያዙ ግማሽ ያክሉ ደግሞ ሞተዋል።

ከ46 አመታት በፊት ከገዳይ ወረርሽኞች አንዱ የሆነው ኢቦላ መጀመሪያ ላይ የተገኘው በሱዳን እና ዛየር ነበር። በርግጥ በስያሜ መድሎ ጥያቄ ቢነሳበትም ስሙን በዛየር ከሚገኘው የኢቦላ ወንዝ ነው ያገኘው። የመጀመሪያው የኢቦላ ወረርሽኝ የሆነው ኢቦላ ሱዳን ከ284 የሚልቁ ሰዎችን አጥቅቷል። የዚሁ ወረርሽኝ የመግደል ምጣኔ 53 በመቶ ያክል ነበር።

ኢቦላ ሱዳን መጀመሪያ የተመዘገበው በ1968 በንዛራ ከተማ የሱቅ ሻጭ በነበረ ሰው ላይ ነው። ይሄው ታማሚ ከአምስት ቀናት በኋላ ከሞተ ከቀናት በኋላ በዚሁ በሽታ ሳቢያ በከተማዋ አንድ ሰው ሞቷል። ከጥቂት ወራት በኋላ ደግሞ ሁለተኛው የኢቦላ ቫይረስ በዛየር ያምብኩ ተገኝቷል። ኢቦላ ዛየር የተሰኘ ስያሜም ተሰጥቶታል። ይሄው የኢቦላ ቫይረስ ከሌሎቹ የኢቦላ ቫይረስ ዝርያዎች ከፍተኛ ገዳይነት የነበረው ነው። የመግደል ምጣኔውም 88 በመቶ ነበር። 318 ያክል ሰዎችም በቫይረሱ መጠቃታቸው ተመዝግቧል።

ሰውነትን በከፍተኛ ሁኔታ በሚያዳክመው የኢቦላ ቫይረስ አንድ ሰው በተለከፈ ከ አራት እስከ 15 ቀናት ባሉት ጊዜያት ምልክቶቹን ማሳየት ይጀምር ነበር። የደም መፍሰስ፣ ከፍተኛ ትኩሳት፣ አጠቃላይ የሰውነት መድከም በሂደትም በሰውነት ውስጥ ደም መፍሰስ፣ የመሳሰሉ ምልክቶችን በተጠቃው ሰው ላይ የሚያደርስ ውስጣዊ የሰውነት ክፍሎችን የሚጎዳ የጊዜው አደገኛ ወረርሽኝ ነበር። ከሰባት እስከ 10 ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ ተጠቂውን በድካም፣ የሰውነት ውስጥ ፈሳሽ መሟጠጥ በማስከተል በድንጋጤ የሚውጥም ነው።

ይሄው መዘዘኛ ወረርሽኝ የከፋ ጠባዩ ደግሞ ከተጠቂው አቅራቢያ ያሉትን ሰዎች ማጥቃቱም ጭምር ነው። በሱዳን ናዝራ በቫይረሱ የተጠቃው ሰው ወንድሙ ታመመ። ወደ ሆስፒታል ተወስዶ ማገገም ቻለ። የወንድሙ የስራ ባልደረባ ግን ታሞ ወደ ሆስፒታል በተወሰደ በሁለት ቀናት ውስጥ ሞቷል። የዚሁ ሰው ባለቤትም ከአምስት ቀናት በኋላ በበሽታው ለሞት ተዳርጋለች።

ከሳምንት በኋላ ጎረቤት የነበረ ሰው ሞተ። ውሎ አድሮ በዚያው ዙሪያ የነበሩ 48 ሰዎች በቫይረሱ መጠቃታቸው ብሎም 27 ሰዎች በዚሁ ሳቢያ መሞታቸው ተመዝግቧል።

የኢቦላ ቫይረስ ልማድን የተመለከቱ ብሎም የሆስፒታል ሰራተኞች የበሽታውን ምልክት ማሳየት በመጀመራቸው የህክምና ባለሙያዎቹ ለመተላለፍ ከተጠቂው የቅርብ ግንኙነት ማድረግን እንደሚጠቀም አስተዋሉ። በደቡብ ሱዳን በማሪዲ ሆስፒታል ከ61 ነርሶች 33ቱ በቫይረሱ ትኩሳት ሞተዋል።

ከሶስት ወራት በኋላ በመጨረሻም የአለም የጤና ድርጅት በቀጠናው የተከሰተውን ወረርሽኝ ለመቆጣጠር እገዛ ማድረግ ጀመረ። ምንነቱ ከተለየ በኋላ የቫይረሱ ተጠቂዎችን ማግለል ስርጭቱን ለመግታት ፍቱን መሆኑ ግልጽ ሆነ። በፍጥነትም የኢቦላ ወረርሽኝ ተገታ። ከ1968 ጀምሮ በተለያየ ጊዜ በተከሰተው የኢቦላ ቫይረስ ብዙ ሰዎችን ለስቃይ ሞት ዳርጓል።

ከኢቦላ ሱዳን እና ኢቦላ ዛየር በመቀጠልም ሶስተኛው ኢቦላ ሬስተን በ1981 በኢቦላ ቫይረስ የተጠቁ ዝንጀሮዎች ሬስተን፣ ቨርጂኒያ ሲገቡ ታውቋል። ጥቂት ሰዎች በዚህኛው ዝርያ መያዛቸው ቢነገርም የደም መፍሰስ ትኩሳት አልያዛቸውም።

በተለያየ ጊዜ በተከሰተው የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ ከ1968 ጀምሮ ከ11 ሺህ በላይ ሰዎችን ሞት አስከትሏል። ብዙው ሞት የተመዘገበው ግን በምእራብ አፍሪካ ነው።

በአብርሃም በለጠ
2022-06-27