የተዛባ የስርዓተ ጾታ ባለበት ማኅበረሰብ ውስጥ ሴቶች ባለተለመደ የስራ ዘርፍ ሲሰማሩ አግራሞትን ያጭራል።
ከባህር ዳር ውብ ዘንባቦች ስር ሴቶች የደንበኞችቻውን ጫማ ለማሳመር ደፋ ቀና ሲሉ ማየት ከባህር ዳር ውጪ ላለ ሰው ነው እንጂ ለከተማዋ ነዋሪ እንግዳ አይደለም።
እነዚህ ታታሪዎች ዝቅ ብለው የመንገደኛውን ጫማ ግርማ ሞገስ ያላብሱታል።
በጫማ ማስዋብ ሙያ ላይ የሚሰማሩ ሴቶች ቁጥር ከወንዶች ጋር ሲነጻጸር አናሳ ነው የሚባለውን አባባል ባህርዳር የምትቀበል አትመስልም።
እዚህ በተቃራኒው ነው ዝቅ የማለትን ጥበብ የተረዱቱ ያደፉትን መራመጃዎች ውበት ይዘሩባቸዋል፤ አቀርቅረው ይኩሏቸዋል።
የትምወርቅ ታሪኩ የ 12ኛ ክፍል ተማሪ ነች። ከሁለት ዓመት በላይ በዚሁ በሊስትሮ ስራ ወይም ጫማ በማስዋብ እየተዳደረች ትምህርቷን ተክታተላለች ።
የትምወርቅ እንደነገረችን ወደዚህ ስራ የገባችው እናቷን ለማገዝ እንደሆነ ትናገራለች
ይህን የስራ ዓይነት ለመጀመር ከሌሎች የስራ ዘርፎች በተለየ መልኩ ውጪው አነስተኛ ነው ባይ ነች
ከማኅበረሰቡ ዘንድ ሴት ልጅ ይህን ስትሰራ ተጸእኖ ይደርስባታል ብላናለች ።
ከአንድ ዓመት በላይ በዚሁ ዘርፍ ልክ እንደ የትመወርቅ ሁሉ የሽሐረግ ጌትነት የተባለችው ወጣት በውቢቷ ባህር ዳር ህይወቷን ትገፋለች።
በርካቶች ይህን ስራ እንዳልሰራ ይመክሩኛል አኔ ግን ነገዬን ለማሳመር ይህንን ዘርፍ መርጫልሁ ትላለች ።
ሁለቱም ባለታሪኮቻችን የሚያገኙትን ገቢ በመቆጠብ ወደ ሌላ የስራ ዘርፍ የመሽጋገር ህልም አላቸው።
አላፊ አግዳሚው ስለሚጫማው ጫማ ውበት ሲጨነቅ እነዚህ ልባቸውን አስቀድመው ያነቁ ብርቱዎች ነጋቸውን አቀርቅረው ይሰራሉ።
ካደፈ ጫማ ላይ የተራማጁን ቀን የነሱን ነገ አዲስ ያደርጋሉ።
በመቅደስ እንዳለ
2022-06-27
