ሀገሬ ቲቪ

የጥላቻ ንግግር

ይህ በእኛዋ አፍሪካ የሆነ ነው። ደጋግመን የሰማነው፣ ዛሬም በልባችን ውስጥ ይፃፍ እና እንማርበት ዘንድ ካለመሰልቸት የምንደጋግመው። ርዋንዳ፤ ረቡዕ መጋቢት 28 1986 ዓ.ም በዋና ከተማዋ ኪጋሊ አንድ አውሮፕላን ተመቶ መውደቁ ተሰማ።

ቀድሞም በገዢዎቻቸው ቤልጄም እና ጀርመን በዘር ተቆጥረው የተለዩት ሯንዳውያን ነገሩ ለፅንፈኞቹ የሁቱ አማፅያን የሚፈልጉትን ለማድረግ የተመቸ አደረገላቸው።

የፕሬዘዳንታችን ገዳዮች ሲሉ ቱትሲዎችን ለሞቱት የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ተጠያቂ አደረጓቸው። በየመገናኛ ብዙኃኖቻቸው ሁሉ ስይቀሩ ማዕድ አብረው የቆረሱ ጎረቤቶቻቸውን ሁሉ እንዲያጠፉ ለማነሳሳት ተጠቀሙበት። የሰው ልጅ እንደ ትንሿ በረሮ ተቆጠሮ እንደ ቅጠል በየሜዳው ረገፈ።

አንድ መቶ ባልሞሉ ቀናት ውስጥ ከ800 ሺሕ የሚልቁ ቱትሲዎች እና ለዘብተኛ ናቸው የተባሉ ሁቱዎች ረግፈው ቀሩ። ይህ ከጥላቻ፣ በአንደበት የዳበረ ኋላም የሰውን ልጅ በየሜዳው ያስቀረ ኩነት ነው።

ይህንን ማንሳታችን ያለምክኒያትም አይደል። ከአትላንቲክ ውያኖስ የባሪያ ንግድ እስከ ምዕራቡ ዓለም የናዚ ጭፍጨፋ፣ ከናይጄሪያ እስከ እሲያዊቷ ሀገር ማይናማር የጥላቻ ንግግር ለበትርካቶች ህይወት መቀጠፍ ምክኒያት ሆኗል።

ለመሆኑ የጥላቻ ንግግር ማለት ምን ማለት ነው ስንል አቶ አሮን ደጎል የህግ እና የአስተዳደር መምህርን ጥይቀናቸዋል።

“የጥላቻ ንግግር ማለት ማንኛውም የአንድን ግለሰብ ሃይማኖት፣ ዘር፣ ባህል፣ የቆዳ ቀለምን ተንተርሶ ጥቃት እንዲደርስበት የሚያደርግ ተግባር ነው።”

ኢትዮጵያም በተለይ በዓለማችን ላይ ፈተና እየሆነ የመጣውን የጥላቻ ንግግርን ይገታል የተባለለት ህግ በ2012 ዓ.ም አውጥታ ወደ ተግባር አስገብታለች።

በህጉም ላይ የጥላቻ ንግግር ለሚለው ቃል ትርጉም ሲሰጥ እንዲህ ይላል።

“የጥላቻ ንግግር” ማለት በአንድ ሰው ወይም በተወሰነ ቡድን ማንነት ላይ ያነጣጠረ፣ ብሔርን፡ብሔረሰብንና ህዝብን፣ ሃይማኖትን፤ ዘርን፣ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ ሆን ተብሎ ጥላቻን፣ መድሎን ወይም ጥቃትን የሚያነሳሳ ንግግር ነው።

ይህ የጥላቻ ንግግር ታዲያ በአጋጣሚ ሊደረግ እንደማይችል አቶ አሮን ጨምረው ያነሳሉ።

“የጥላቻ ንግግር በአጋጣሚ የሚደረግ አይደለም። አድራጊው ሆን ብሎ በጠላው ሰው ላይ ጉዳት እንዲደርስ ሌሎችምን የሚያነሳሳበት ተግባር ነው።”

የጥላቻ ንግግርን በህግ የከለከሉ ሀገራት አሁን ቁጥራቸው 36 ደርሷል። ይህንን ሁሉ የተባለለት የጥላቻ ንግግር ከምን ይነሳ ይሆን ስንል ጥያቄያችንን ለአቶ አሮን አቀረብን።

“የጥላቻ ንግግር ከጥላቻ የሚመነጭ ነው። የጠላነውን ሰው ጥቃት እንዲደርስበት በራሳችን ወይንም በሌላ ወገን እንዲጎዳ፣ እንዲፈናቀል ወይም እንዲገደል ለማድረግ ስናነሳሳ።”

አሁን ሀገራችን ላለችበት ምስቅልቅል የዳረጋት የዘመናት የጥላቻ ንግግር ውጤት ነው የሚሉት አቶ አሮን የጥላቻ ንግግርን ለማስቀረት መቅደም አለበት ስለሚሉት ነገርም አንስተዋል።

“ህግ ከማውጣት በላይ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል።”

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ባለፈው ዓመት በነበረው አመታዊ ስብሰባው ላይ የጥላቻ ንግግር በዓለም ላይ እያደረሰ ያለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ ይረዳ ዘንድ በየዓመቱ ሰኔ 11 ቀን የዓለም አቀፍ የጥላቻ ንግግርን የመከላከል ቀን ተደርጎ እንዲከበር ወስኗል።

ቀኑ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ግዜ የተከበረ ሲሆን የጥላቻ ንግግር እየጨመረ ነው በሚል መሪ ቃል ታስቦ ውሏል።

በተለይ የማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች በማህበረሰቡ መሀል የጥላቻ ንግግሮችን እያስፋፉ ስለመሆናቸው ያነሱት የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እነዚህን ድርጊቶች መከላከል እንደሚገባ አሳስበውል።

በሳምሶን ገድሉ
2022-06-28