ሀገሬ ቲቪ

የሲቪል ሰርቪስ ሳምንት ሊከበር ነው

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን መስሪያ ቤት እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በጋራ በመሆን የፊታችን ሀሙስ ለሚያከብሩት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። “ንቁ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለሰላም ለዲሞክራሲና ለልማት” በሚል መሪ ቃል ለሁለተኛ ጊዜ የሚዘጋጀው ክብረ በዐል መብትና ግዴታውን በውል የተረዳ በውይይትና በምክንያታዊነት የሚያምን የነቃ እንዲሁም በነጻነት የተደራጀ ማህበረሰብ ለመፍጠር መሆኑን በመግለጫው ተመላክቷል።

መግለጫውን የሰጡት የሰቪል ማህበረሰብ ባለስልጣን ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ድርጅቱ በአዲስ ከተቋቋመ በኋላ በግልፅነት ያልተቀመጡ አዋጆችን በማንሳት በአዲስ የመተካት ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የማህበረሰቡን መብቶች ለማስከበር የቆሙ እንደመሆናቸው መጠን የሰሞኑን አሰቃቂ የዜጎች ሞት እንዲሁም መፈናቀልን በዘላቂነት ለመፍታት ምን እየተሰራ ነው ለሚል ከመድረኩ ለተነሳው ጥያቄ የሲቪል ሰርቪስ ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሔኖክ መለሰ በጉዳዩ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰሩ መሆኑን አመልክተዋል ።

ከሰኔ 23 እስከ ሰኔ 25 በሒልተን ሆቴል ለሁለተኛ ጊዜ የሚከበረው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት የፓናል ውይይቶች ኤግዚቢሽን እንዲሁም የመገናኛ ብዙኋን መርሀ ግብሮችን ያካተተ ሲሆን ማንኛውም ስው በመምጣት በበዓሉ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

በዮሴፍ ከበደ
2022-06-28