የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የውቅያኖስ ጉባኤን ከሰኔ 20 ጀምሮ በፖርቱጋሏ ሊዝበን ከመላው ዓለም የመጡ መሪዎች በተገኙበት እያካሄደ ነው።
“ውቅያኖሶችን አናድን፣ የወደፊት ሕይወታችንን እንጠብቅ” በሚል መሪ ቃል የተጀመረው ይህው ጉባኤ እስከ ሐምሌ 1 ይቀጥላል።
የዘንድሮውን የውቅያኖስ ጉባኤ የኬንያና የፖርቱጋል መንግሥታት በጋራ አሰናድተውታል።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉተሬስ እንደገለጹት “ውቅያኖስ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሕይወታዊ ሀብት ላይ ለሚደርሰው ጉዳትና ብክለት በፕላኔቶች ላይ ለሚደርሱ ችግሮች ምላሽ በመስጠት ረገድ ትልቁ አጋራችን ሊሆን ይችላል” ብለዋል።
ውቅያኖስ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን የፕላኔቷን ክፍል የሚሸፍን ሲሆን ፤የሰው ልጆችንም ሆነ በምድር ላይ ያሉ ሌሎች ሕያዋን ፍጥረታትን በሙሉ የሚደግፈው የሕይወት ምንጫችንም ነው።
ውቅያኖሱ ቢያንስ 50 በመቶ የሚሆነውን የፕላኔቷን ኦክሲጅን ያመርታል በዚህ የተነሳ የአብዛኛው የምድር ህይወታዊ ሀብት መኖሪያ ነው። በዓለም ዙሪያ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ዋነኛ የፕሮቲን ምንጭ ነው። በ2022 ዓ.ም ወደ 40 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በውቅያኖሶች ላይ በተመሠረቱ ኢንዱስትሪዎች ተቀጥረው የሚሠሩበት ውቅያኖስ ለኢኮኖሚያችን ቁልፍ ነው። በርካታ ጥቅሞች ቢኖሩትም በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ድጋፍ ያስፈልገዋል ተብሏል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ፀሀፊ ሊዩ ዠንሚን ቀኑን አሰመልክተው ባስተላለፉት መልዐክት እንደገለጹት ከሆነ
“በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወታቸውን አሊያም ስራቸው የተመሰረተው በውሃ ላይ ነው እንዲሁም ውቅያኖስ ለበርካታ የውሃ አካላት እና ብዝሃ ህይወት መኖሪያም ነው፤ነገር ግን በሰዎች እንቅስቃሴ ውቅያኖሶቻችን አደጋ ላይ ናቸው።”
ይህንን መሰረት በማድረግ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ በ2022ዓ.ም. 80 በመቶውን የባህር ወለል ካርታ ለማውጣት ዓለም አቀፍ ጥረት መደረግ አለበት ብለዋል።
ጉተሬስ በፖርቱጋል ዋና ከተማ በ2022 በተባበሩት መንግሥታት የውቅያኖስ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ንግግር ሲያደርጉ በዓለም ዙሪያ ያሉ መንግሥታት
“ውቅያኖስን መልሶ የማግኘት ምኞታቸውን እንዲያሳድጉ” ጥሪ አቅርበዋል።
“ሕይወታቸው በባሕር ላይ የተመካ ሰዎችን ከአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለመጠበቅ” የሁሉንም ዓይነት ብክለት መቀነስ ላይ ማተኮር አለበት ብለዋል።
አዲስ የአየር ንብረት-የሚቆጣጠረው የባሕር ዳርቻ መሠረተ ልማት መፈጠር አለበት እንዲሁም የባህር ትራንስፖርት ዘርፍ በ 2042 ዓም የካርቦንል ልቀትን ወደ ዜሮ ለመቀነስ ቃል መገባት አለበትም ሲሉ አሳሰበዋል።
የፖርቱጋሉ ፕሬዝዳንት ማርሴሎ ሬቤልዮ ደሱሳ የባህር ክልል ካርታ እንዲሰራ እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ ትምህርት ላይ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ፈሰስ እንዲደረግ ጠይቀዋል። የቪዲዮ መልዕክት ያሰተላለፉት የተመድ ዋና ፀሐፊ ልዩ ልኡክ ፒተር ቶምሰን በበኩላቸው
“የዚህን ፕላኔት የህይወት ድጋፍ ስርዓት ማጥፋታችንን አቁመን የሰው ልጅ ከውቅያኖስ ጋር ያለውን ግንኙነት መመለስ አለብን።”
የፖርቹጋል መንግሥት ውቅያኖስን መጠበቅ የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት፣ የሕይወታዊ ሀብትን እና ዘላቂ ልማትን ለማስፋፋት እንዲሁም የባህር ደህንነትእና የመንቀሳቀስ ነፃነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው ሲሉ ፕሬዝዳንት ኮስታ ተናግረዋል።
በፍሬህይወት ታደሰ
2022-06-28
