ሀገሬ ቲቪ

ድብን ያባረረችው ድመት

መቼም አንዳንዴ የምንሰማቸው ነገሮች ወቸው ጉድ ሳያሰኙን አያልፉም። በዚህ ዓለም የተፈጠሩ ፍጥረታት በሙሉ የራሳቸው ግብር እና የራሳቸው መለያ ባለቤት ናቸው።

ለምሳሌ ያህል አንበሳን የጫካ ንጉስ ስንል እንጠራዋለን። በጫካ ውስጥ የሚገዳደረው የለምና ነው። አቦሸማኔን ደግሞ በፍጥነት የሚወዳደረው እናጣለታለን።

እንዲህ እንዲያ እያልን ብንጠራ ለእያንዳዱ የራሳቸው የሆነ ግርማሞገስ ባለቤት ሆነው እናግኛቸዋለን።

ታዲያ የቤት እንስሳዋ የዱሩን አቻየለሽ ቆሌውን ገፋ አባራዋለች መባሉን ሰምተናል።

ነገሩ ምንም ብቀጥን ጠጅ ነኝ ይሉት አይነት ነው። አንዲት ድመት በመጠንም በክብደትም በብዙ እጥፍ የሚበልጣትን ድብ አሳዳዋለች። ወዳጃችን እንደሚታወቀው የድመት እና የድብ መጠን ከቶውንም የሚወዳደር አይደለም። ነገሩ የሆነው በብሪቴይን ኮሎምቢያዊ ሰው ነው የድመቱን ገድል ቀርጾ ተደመሙ ሲል ያጋራው።

የድመቷ ገድል አንድ በመቶዎች እጥፍ ክብደት የሚበልጣትን ድብ ግብግብ ገጥማለች። ምነው ካሉም ይህችው ፍርሃት እንደትቢያ የበነነላት ድመት ከባለቤቶቿ ጋር ሳለች የመጣውን ድብ ነው ከመንገዳችን ዞር በል ስትል ወደ ማሳደዱ ያመራችው።

ወንድማማቾቹ ጋቪን እና ስቱሮክ ይህችን ድመት የነብር ልብ ተላበሽ ሲሉ ታይገር ብለው ሰይመዋታል። ነብሪት ድመቷ ታዲያ ከድቡ በፊትም የጎረቤቶቿን ውሾች በማሳደድ ዝናን መጎናጸፏ ይነገርላታል።

ወንድማማቾቹ የተዝናኖት ጉዞ ለማድረግ ለመኪና ጉዞ ሲዘገጃጁ ነው ግዙፉ ጥቁር ድብ ያጋጠማቸው። ታይገር የተሰኘችው ድመት ታዲያ ድቡን ባየችው ቅጽበት ከመሸሽ ይልቅ መፋለምን ምርጫዋ አድርጋለች።

ከባለቤቷ ጋቪን የተይ ተመለሽ ጥሪን አሻፈረኝ ያለችው ድመቷ ግብ ግቡን ተያያዘችው። በሌላ በኩል ነይ እያለም ቢሆን ባለቤቷ የድመቷን ገድል በስልኩ ለማስቀረት ችሏል።

ግዙፉ ድብ ከትንሽየዋ ታይገር የገጠመውን ፍልሚያ መቋቋም አልቻለም። ኋላም መሮጥን ምርጫው አድርጓል ሲል ግሎባል ኒውስ አስነብቧል።

ቀድሞም ጎረቤት ውሾች ላይ ልቧን ያፈረጠመችው አሁን የዱር ጥቁር ድብ ማሳደዷ የተሰማው በጎረቤቶቿ ቡችሎች ስትለማመድባቸው በመቆየቷ ይሆን?

በሳምሶን ገድሉ
2022-06-28