የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ን ለመቀላቀል ፊንላንድ እና ስዊድን ጥያቄ ሲያቅርቡ ቢቆዩም የኔቶ አባል የሆነችው ቱርክ ሀገራቱ እንዳይቀላቀሉ ተቃዋሚ ሆና ቆይታለች።
ለደህንነቴ እና ለኔቶ የወደፊት እጣ ፋንታ ስል ነው ፊንላንድ እና ስዊድን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የአባልነት ጥያቄ ላይ አቋም የያዝኩት ያለችው ቱርክ በሀገራቱ ላይ የነበረኝን ተቃውሞ ማንሳቴን እወቁልኝ ስትል ያቋም ለውጥ ማድረጓን አሳውቃለች።
በማድሪድ ወታደራዊ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የኔቶ አባል እንዲሆኑ ለማድረግ ከቱርክ ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ኔቶ በስፔን ዋና ከተማ የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሴፕ ጣይብ ኤርዶጋን፣ የፊንላንዱ ፕሬዚዳንት ሳዉሊ ኒኒስቶ እና የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር ማግዳሌና አንደርሰን ባደረጉት ስብሰባ ነው የሶስትዮሽ ስምምነት ላይ የደረሱት።
የኔቶ ዋና ጸሃፊ የንስ ስቶልተንበርግ በስምምነቱ ላይ ይህንን ብለዋል።
“ፊንላንድ እና ስዊድን ወደ ኔቶ እንዲቀላቀሉ መንገድ የሚከፍት ስምምነት መደረሱን በማወጄ ደስ ብሎኛል”
ዋና ጽሃፊው አክለውም ቱርክ ከዚህ ቀደም ስጋት ይገባት የነበረው የሽብርተኝነት ጉዳይ መላ ተብጅቷል ሲሉ ተደምጠዋል።
“ፊንላንድ እና ስዊድን የጦር መሳሪያ ወደ ውጭ መላክ እና ሽብርተኝነትን በመዋጋት ዙሪያ የቱርክን ስጋቶች የሚመለከት ስምምነት ተፈራርመዋል”
የስዊድኗ ጠቅላይ ሚኒስትር አንደርሰን በበኩላችው ስምምነቱን “በጣም ጥሩ ስምምነት” ሲሉ አወድሰውታል።
“ስምምምነቱ ጥሩ ስምምነት ነው። ቱርክ እገዳዋን እንድታነሳ ለማሳመን ስዊድን ስትለማመጥ ከርማለች የሚለውን ክስ ግን አንቀበልም ”
የስዊድን እና የፊንላንድ መሪዎች ረቡዕ እና ሐሙስ በኔቶ ጉባኤ በአባል ሀገራት በማፅደቅ ወደ ሙሉ አባልነት ይገባሉ።
በታሪክ ውስጥ የስዊድን እና ፊንላንድ ኔቶን የመቀላቀል ፍላጎት አሽቆልቁሏል።
ይህ የሆነውም ሃገራቱ ከሩስያ ጋር ባላቸው የጸጥታ እና ደህንነት ግንኙነት ላይ ግልጽ ያልሆነ አቋም በመኖሩ ነው።
ይሁንና ግን የሩስያ ዩክሬይን ጦርነት ሃሳባቸውን በፍጥነት ቀይረው ኔቶን የመቀላቀል ጥያቄ እንዲያቀርቡ ምክንያት ሆኗል።
የቱርኩ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶኻን ሃገራቱ የኩርድ ሰራተኞች ፓርቲ (ፒ ኬ ኬ) ደጋፊዎች ናቸው በሚል ሲወንጅሏቸው ቆይተዋል።
ስዊድን 100,000 የኩርድ ስደተኞች መኖሪያ እንደሆነች ይነገራል።
ቱርክም ከኩርድ አማጺያን ጋር ግንኙነት አላቸው ያለቻቸውን ግለሰቦች አሳልፋ እንድትሰጥ ጠይቃለች።
ፊንላንድ እና ስዊድን ቱርክ የፈለገችውን የፀረ-ሽብርተኝነት ማረጋገጫ ለመስጠት የአገር ውስጥ ህጋቸውን ሳይቀር ለማሻሻል ሳይቀር ተስማምተዋል።
ማሻሻያውም ሽብርተኞችን ለቱርክ አሳልፎ መስጠትን ሊያጠቃልል ይችላል ሲል ዘ ጋርዲያን ጽፏል።
የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ስዊድን እና ፊንላንድ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል እንዲሆኑ የቱርኩን ፕሬዝዳንት እያግባቡ ነው እየተባለ ሲወራ ነበር ።
ልፋታቸው የሰመረ ይመስላል።
ቦሪስ ጆንሰን በትዊተር ገፃቸው የስዊድን እና የፊንላንድ አባልነት ጥምረታችን የበለጠ ጠንካራ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ያደርገዋል ሲሉ ጽፈዋል።
ስዊድን እና ከሩሲያ ጋር 1 ሺ 300 ኪሎ ሜትር የምትዋሰነው ፊንላንድ የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶን የሚቀላቀሉ ከሆነ ሩሲያ የኑክሌር ጦር መሳሪያንና ሃይፐር ሶኒክ ሚሳኤልን ወደ መሃል አውሮፓ ልታንቀሳቅስ እንደምትችል ማስጠንቀቂያ መስጠቷ አይዘነጋም።
በመቅደስ እንዳለ
2022-06-29
